ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ( ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አቶ ጃዋር ሞሀመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ ቦረና እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ዛሬ ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና በህገመንግስት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ያሉት አቶ ጃዋር አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ መስጠታቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግባለች፡፡

በዚህም የኦርቶዶክስ እምነት አባቶችን ለማስገደል እየተንቀሳቀሰ ነበር የሚል የወንጀል ክስ ቀርቦብኛል ያሉት ተከሳሹ እንዲህ ያለ ነገር ለማድረግ ማንነቴም የኋላ ታሪኬም አይፈቅድም ብለዋል፡፡ አክለውም ወላጅ እናቴ የኦርቶዶክስ እምነተት ተከታይ ናት ኦርቶዶክስ ላይ ጥቃት እንዲደርስ አደረኩ ማለት የእናቴ ወገኖች ላይ ወይንም ግማሽ አካሌ ላይ ጥቃት እንዳደረስኩ ነው የሚቆጠረው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የብሄር ግጭት ለማስነሳት እና መንግስተትን በትጥቅ ትግል ለመጣር ሲሰሩ ነበር የሚል ክስ የቀረበባቸው አቶ ጃዋር ባለፉት አመታት ሳደርግ የነበረው የፖለቲካ ትግል ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ሳይሆን እንደውም ለማስማማት ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል እንጂ የትጥቅ ትግል አድርጌ እንደማላውቅ ደግሞ ከሳሾቼ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያውቁታል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሸ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሀምዛ ቦረና እንዲሁም ሌሎች ሁለት በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተመሳሳይ መልኩ ወንጀሉን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አየይደለንም በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡፡

ይህን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮቼን እንዳሰማ እና ማስረጃዎቼን እንዳቀርብ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡

ችሎቱ ምስክሮችን ለመስማት ለመጋቢት 29 ቀን ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ከዛ በፊት ግን አቃቤ ህግ በምስክሮች እና ወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ምስክሮቹን በዝግ ችሎት ለማሰማት ያቀረበው አቤቱታ ላይ መጋቢት 28 ውሳኔ ለመስጠት ችሎቱ ቀጠሮ ይዟል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ከ1 እስከ 3 ካሉት ተከሳሾች ውጪ ያሉት ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብትን የሚያስነፍግ ባለመሆኑ ችሎቱ ዋስትና መብታቸውን እንዲያስክብርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱ በዚህም ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ለመመስጠጥ ደግሞ ለ መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓም ቀጠሮ ይዟል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]