PM Hailemariam Desalegn
PM Hailemariam Desalegn
  • በድንበሩ ግጭት ዙሪያ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከባንኪሙን ጋር ዛሬ ይነጋገራሉ

ዋዜማ ራዲዮ- ኤርትራ  የተፈፀመብኝን ወረራ የፀጥታው ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲመለከት ስትል ትናንት ማመልከቻ አስገባች።

ኤርትራ ማመልከቻዋን ከማስገባቷ ቀደም ብሎ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ቃል አቀባይ በድንበር ግጭቱ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

እንደ ቃል አቀባይዋ ስቴፈኒ ጃሪክ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተጫረው ግጭት ያሳሰባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ይነጋገራሉ። ባን ኪሙን እና ኃይለማርያም የሚገናኙት ሁለቱም በሚሳተፉበት እና በቤልጄየም  ዛሬ በሚጀመረው የአውሮፓ የልማት ጉባኤ ጎን በተዘጋጀ የሁለትዮሽ ስብሰባ ነው። በስብሰባው ለመገኘት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወደ ብራስልስ አቅንተዋል።

ጃሪክ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የባን ኪሙን እና ኃይለማርያም ስብስባ ግጭቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም በምክክራቸው ጊዜ የወቅቱ ቀውስ ከመነጋገሪያ ነጥቦች አንዱ ይሆናል። የተባበሩት መንግስታት ጉዳዮን አስመልክቶ በተለያዩ ደረጃዎች ከሚገኙ አካላት ጋር መነጋገሩን የጠቆሙት ቃል አቃባይዋ ዝርዝሩን ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

“በድንበር አካባቢ ስላለው ውጊያ የሚወጡ ሪፖርቶች ዋና ጸሐፊውን አሳስቧችዋል” ይላሉ ቃለ አቃባይዋ  ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ። “ዋና ጸሐፊው ሁለቱም መንግስታት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና ልዩነቶቻቸውን በሰላም እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።”

አሜሪካ በፊናዋ “ስሞኑን የተፈጠረው የድንበር ግጭት አሳስቦኛል፣ ሁለቱም ሀገሮች ከሀይል እርምጃ ይልቅ በድርድር መፍታት ይገባቸዋል” ስትል ማክሰኞ አመሻሹን መግለጫ አውጥታለች።

የአፍሪቃ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤትም ግጭቱ እንዳሳሰበው በመግለፅ ሁለቱ ሀገሮች ከትንኮሳ እንዲታቀቡ ጠይቋል።

ለእንደዚህ አይነቱ ጥሪ የተሰጠ ምላሽ በሚመስል መልኩ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኦፊሴሊያዊ የትዊተር ገጻቸው ተከታዩን ትናንትና ፅፈው ነበር። ” ‘ሁለቱም ወገኖች መታቀብ እንዳለባቸው’ ጥሪ የሚያቀርቡ አሰልቺ መግለጫዎች ውጤት አልባ ናቸው” የሚሉት የማነ “ያለምንም ማወላወል የህወሓት የወረራ ድርጊት ሊወገዝ ይገባል” ባይ ናቸው።