Eritrea President Isaias Afeworki
Eritrea President Isaias Afeworki

ይህ ዘገባ በኤርትራ ወገን ስላለው ሁኔታ የሚያብራራ ነው።ከኢትዮጵያ ወገን ያሰባሰብነው መረጃ ከስር ባለው ማስፈንጠሪያ ይመልከቱት።

ዋዜማ ራዲዮ- የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በፆረና ግንባር ወረራ ፈፅሞብኛል ሲል መግለጫ ስጥቷል። በኤርትራ በኩል ስላለው ሁኔታ ከአካባቢው ምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ኤርትራ ተጨማሪ ሀይል ወደ ግጭቱ ቦታ ማንቅሳቀስ ጀምራለች።

ዓዲ መስገነን አኻራንን ቁኒቁንቶን በተባሉ ቦታዎች ሰኔ 4, 2008 በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ኃይሎች መካከል ወታደራዊ ግጭት እንደተካሄደ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስቴር ምንጮቻችን ገልፀውልናል።

ይህ ከእኩለሌሊት በኃላ ማለትም ከሌሊቱ 6:45 የተካሄደው የሁለቱ ወገኖች የተኩስ ልውውጥ ወታደራዊ ቃኚን ያሳተፈ ሲሆን እስከ ጧቱ 9:45 ድረስ ቀጥሎ አድሯል።

በዚህ ግጭት ከኤርትራ በኩል በብዛት ከወታደራዊ  ቃኚ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ቆየት ብሎ ግን ሌላው የሰራዊቱ ክፍልም ተቀላቅሏል። በኢትዮጵያ ወገንም የወታደራዊ ቃኚ እና ህዝባዊ ሚሊሻዎች የተሳተፉበት ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ግጭት ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ ከነበሩት የሚለይበት ሞርታር እና አርፒጂን በመሰሉ ቀላል የጦር መሳሪያዎች መታገዙ እንደሆነ የመከላከያ ምንጮቻችን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዛሬ ንጋት ላይ ማይውራይ በተሰኘው አካባቢ የሚገኙ የኤርትራ የከባድ መሳሪያ ክፍለጦሮች ግጭቱ ወደተፈጠረበት ሥፍራ እንደተጠጉም ለማወቅ ተችሏል።

የኤርትራ መንግሥት ለሁሉም ክፍለጦሮች የኢትዮጵያ መንግሥት ወረራ የማካሄድ ዕቅድ እንዳለው ሲገልፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የቀደመ ሪፖርታችንን በማስፈንጠሪያው ይመልከቱ። http://wazemaradio.com/?p=2296