• አስዋን ግድብ ሲጎድል የሕዳሴው ግድብ ውሀ መሙላቱን ያቆማል –ግብፅ ያቀረበችው እቅድ
  • እያወዛገበ ባለው በሕዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ላይ ነገና ከነገ ወዲያ ውይይት ይደረጋል
Minster Sileshi Bekele- Photo- Fortune Addis

ዋዜማ ራዲዮ- ግብፅ የሕዳሴው ግድብ የውሀ አሞላልን በተመለከተ አዲስ ዕቅድ ማቅረቧን ተከትሎ የሱዳን የኢትዮጵያና የግብፅ ሚንስትሮች ለድርድር ይቀመጣሉ። ሲጀመር ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት የዲፕሎማሲ የበላይነቱን በያዘችበት ወቅት የተዘጋ አጀንዳ እንዴት እንደ አዲስ ለውይይት ክፍት ተደረገ የሚል ጥያቄ ይነሳል። አሁንስ በሚደረገው ድርድር ምን ሰጥተን ምን ለመቀበል ተዘጋጅተናል? ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የመንግስት ባለስልጣናትንና ባለሙያዎችን አነጋግራ ያዘጋጀቸውን ዘገባ አንብቡት።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሀ አሞላል ላይ ከነገ እሁድ መስከረም 4 2012 አ.ም ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የግብጽ ; የሱዳንና የኢትዮጵያ ውሀ ሚኒስትሮች በካይሮ ይወያያሉ።የኢትዮጵያ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለም ለዚሁ ጉዳይ ወደ ካይሮ የሚያቀኑ ይሆናል።ሱዳንም አዲስ ባገኘችው የውሀ ሚኒስትር ያሲር አባስ መሀመድ ተወክላ የኢትዮጵያን ጨምሮ ከግብጹ የውሀ እና መስኖ ሚኒስትር መሀመድ አብደል አቲ ጋር ነው ውይይቱ የሚደረገው።


     የካይሮው ስብሰባ ምናልባትም በህዳሴው ግድብ የውሀ አሞላል ላይ የስምምነት ፊርማ ሊካተትበት እንደሚችል ምንጮቻችን ነግረውናል።ሆኖም ኢትዮጵያን የወከሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቢቻል በግድቡ ውሀ አሞላል ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር አዲስ ሀሳብ ቢያቀርቡ ካልሆነ ደግሞ አሁን ለውይይት የተያዘው አጀንዳ ላይ በፍጹም ከስምምነት መድረስ የለባቸውምም ብለውናል።

     ነገ በካይሮ በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ላይ ውይይት የሚደረገው የግብጹ የውሀ ሚኒስትር መሀመድ አብደል አቲ ከወር በፊት የሀገራቸውን እቅድ ካቀረቡ በሁዋላ ነው።አብደል አቲ በዚህ ባቀረቡት ሰነድ ውስጥ ኢትዮጵያ ግድቡን በሰባት አመት እንድትሞላ የሚጠይቅና ሌሎች ሀሳቦችም የተነሱበት ነው።በኢትዮጵያ በኩልም እነዚህ የካይሮ ፍላጎቶች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን የሚያሳዩ ምላሾች ተሰጥቷቸዋል።እነዚህ በእንዲህ እያሉ ነው የነገው የሶስትዮሽ ውይይት የሚካሄደው።

     ነገር ግን ነገ እሁድ በካይሮ ውይይት ከሚደረግባቸው ነጥቦች ውስጥ በኢትዮጵያ ሙያተኞች ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የግድቡን ውሀ አሞላል አስመልክቶ ከግብጽ ጋር ለሚደረገው ውይይት በዋና ነጥቦች ላይ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት መካከልም ከስምምነት አለመደረሱን ሰምተናል።

     አንዱ የግብጹ አስዋን ትልቁ ግድብ የውሀ መጠን የትኛው ርዝመት ድረስ ሲወርድ ነው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ መያዝ አቁሞ ለግብጹ ግድብ ውሀ የሚለቀው የሚለው ላይ ነው።

ግብጽ ያቀረበችው ሰነድ ላይ የአስዋን ግድብ ውሀ ከመጠኑ ወርዶ ከባህር ጠላል በላይ 165 ሜትር ላይ ከደረሰ ግድቡ ችግር ውስጥ ይወድቃል ይላል። ባለሙያዎቹ ይሄንን critical level ይሉታል። ይህ ማለት የግድቡ ውሀ በተባለው ደረጃ ከሆነ ግድቡ ሀይል ለማንጨት እና ለሌላ ተግባራት ስለሚቸገር ለመጠባበቂያ ያስቀመጠው ውሀን ወደመጠቀም ይገባል።ስለዚህ አስዋን ግድብ መጠኑ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ ሲደርስ ግብጽ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የኢትዮጵያ ግድብ ውሀ መልቀቅ ብቻ ይሆናል ስራው ይላል የካይሮ ሰነድ።ነገም ውይይት የሚደረግበት አንዱ አጀንዳ ይሄው ነው።

      የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ግን ይህ በፍጹም መሆን የለበትም እያሉ ነው።አንደኛ አስዋን ግድብ የውሀ መጠኑ ከባህር ጠለል በላይ 165 ሜትር ላይ ከሆነ ግድቡ መያዝ የሚችለውን 80 በመቶ ውሀ ያዘ ማለት በመሆኑ ግብጽን ምንም አይነት ችግር ውስጥ አይጨምራትም።

የተባለው ቢሆን እንኳ ኢትዮጵያ የግብጽን ግድብ የምትቆጣጠርበት መንገድ ስለሌለ እንዲህ አይነት ግዴታ ውስጥ መግባት የለባትም በሚል ነው። በሌላ በኩል ከአስዋን ትልቁ ግድብ ቀጥሎ ግብጽ በርካታ ውሀ ማከማቻ ያላት በመሆኑ የግድቡን ውሀ ወደነዚህ ማጠራቀሚያዎች እየለቀቀች ሁሌም የአስዋን ግድብ የውሀ መጠን የስጋት ደረጃ ላይ ነው ብትል ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም።

ስለዚህም ኢትዮጵያ የአስዋን ግድብ ከፍታ ከባህር ጠላል በላይ ከ165 ሜትር ዝቅ እንዳይል በሚል የህዳሴ ግድብ ውሀን በመልቁቅ ላይ ተጠምዳ በከፍተኛ ወጭ እያሰራች ያለው ግድብ ለሀይል ማመንጫ የሚሆን ውሀን መያዝ እንዲያዳግተው የሚያደርግ ግዴታ ውስጥ በፍጹም መግባት የለባትም ሲሉ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር ለሙያዎች ይገልጻሉ ።ነገር ግን በከፍተኛ የመንግስት ስልጣናት በኩል የሙያተኞቹን ሀሳብ በማጥላላት ከካይሮ ጋር የመስማማት አዝማሚያ እየታየ ስለሆነ በፍጹም ወደ ስምምነት እንዳይገባበትም ብለውናል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአመት በትንሹ ምን ያክል ውሀ ይልቀቅ የሚለውም በሁለቱ ቀን የሶስትዮሽ ስብሰባ ላይ የሚደረግበት ሲሆን በመጠኑ ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ ተብሏል። ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአመት በትንሹ ከ30 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በላይ ለመልቀቅ መስማማት የለባትም። ግብጽ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በትንሹ በየአመቱ እንዲለቀቅላት ነበር ከዚህ ቀደም የጠየቀችው።ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግድቡ በአመት 35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ለመልቀቅ ነበር የታቀደው።

ነገር ግን ይህም ቢሆን የአየር ሁኔታ አስተማማኝ ሳይሆን ድርቅ ሊኖር ስለሚችል ከ30 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሀ በላይ ለመልቀቅ ከግዴታ ውስጥ መገባት የለበትም።የአባይ ወንዝ እስከዛሬ ድረስ ከ29 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በታች አመታዊ ፍሰት ተመዝግቦበት ስለማያውቅ በ30 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ መስማማቱ ብዙም አይከፋም። እርግጥ ባለፈው አመት ኢትዮጵያ 35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በትንሹ በአመት ለመልቀቅ የተስማማች ቢሆንም ስምምነቱ በግብጽ በኩል ውድቅ የተደረገ በመሆኑ እንደገና በሌላ ሀሳብ ለመወያየት ያመቻል።

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በቀውስ በተጠመደችበትና መንግስት ትኩረቱን የሚሻሙ አጀንዳዎች በበዙበት ወቅት ለግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት በር ሳይከፍት አልቀረም። ለዚህም ይመስላል የግድቡ ጉዳይ ላይ የሚያማክሩ ባለሙያዎች በድርድሩ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት የሚሉት። ባለስልጣናቱ ግን የባለሙያዎቹን ስጋት ቁብ የሰጡት አይመስልም። [ዋዜማ ራዲዮ] Follow Wazema on Twitter @Wazemaradio