በኢትዮጵያና የኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአስር ወራት በኋላ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ፈታኝ ሆኗል። የሁለቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች በድብቅ እስከመገናኘት ደርሰዋል። በኤርትራ ያለውን ውስጣዊ ቀውስ ተከትሎ ድንበሩ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ሲሆን የዋዜማ ዘጋቢ ድንበር አካባቢ ስላለው ሁኔታም ተጉዞ ተመልክቷል። አንብቡት

ዋዜማ ራዲዮ- ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች በደረሱት የሰላም ስምምነት መሰረት እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች ላይ አለመግባባት መከሰቱንና ጉዳዩን ለመፍታት አዲስ ጥረት መጀመሩን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ በወደብ በንግድና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ሰነድ አዘጋጅታ ብታቀርብም ለስድስት ወራት ያህል በጉዳዩ ላይ ከኤርትራ ወገብ አጥጋቢ ምላሽ ሳይገኝ ቆይቷል።

ሁለቱ ሀገሮች ካልተግባቡባቸው ጉዳዮች አንዱ የአልጀርስ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ሲሆን፣ ኤርትራ ስምምነቱ ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንዲሆን ትፈልጋለች። ይሁንና የካሳ ኮምሽኑን በአስመራ ላይ የሚጥለውን ክፍያ ለመፈፀምና ሌሎች ጉዳዮችንም ወደፊት ለማራመድ ዳተኝነት ታይቶባታል።

የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ኦስማን ሳለህ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ከቀናት በፊት በድብቅ አዲስ አበባ መጥቶ የተወያየ ሲሆን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድንም በተመሳሳይ በኣአስመራ ቆይታ አድርጎ ተመልሷል። ወትሮ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ሲያገኝ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ጉብኝት ለምን በምስጢር እንዲሆን እንደተመረጠ ግልፅ አልሆነም።

በድርድሩ ከኤርትራ በኩል ግልፅነት የሚጎድላቸውና ለአፈፃፀም ምቹ ያልሆኑ ሀሳቦች ቀርበዋል፣ ይህንንም መልክ ለማስያዝ ለድርድሩ የተሰየሙ የልዑካን ቡድን አባላት መላልሰው ማየት ነበረባቸው። ማስተካከያዎች ተደርገው በድጋሚ እየታየ ነው። ድርድር ስለሆነ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በጉዳዩ ላይ በንቃት እየተሳተፉ ስለሆነ የተጋነነ ልዩነት የለንም ይላሉ ድርድሩን በቅርብ የሚያውቁ የዋዜማ ምንጭ።

የድንበር ላይ ንግድና የፀጥታ ጉዳይ የሁለቱን ሀገራት ፈታኝ ሁኔታ ላይ የጣለ ሲሆን ኤርትራ ድንበሯን ሙሉ ለሙሉ እንድትዘጋ አድርጓታል።

ወደ ድንበር አካባቢ የተጓዘው የዋዜማ ዘጋቢያችን በድንበር ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ህግ አስከባሪዎችን አነጋግሯል። አንድ የኤርትራ ናቅፋ ሁለት የኢትዮጵያ ብር ይመነዘራል። ይህ የምንዛሪ ልዩነት ኤርትራውያኑ የተለያዩ በውጪ ምንዛሪ የሚገዙ ሸቀጦችን በተለይም ነዳጅን በተሻለ ዋጋ ከኢትዮጵያ እንዲሸምቱ አስችሏቸዋል። ከአስመራ ወደ ትግራይ ይገባ የነበረው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ግን በምንዛሪ ልዩነቱ ሳቢያ መቀዛቀዝ አሳይቷል።

ድንበሩ ከተዘጋ በኋላም ንግዱ ሙሉ በሙሉ አልቆመም። በጋማ ከብቶች በመታገዝ በሌሊት ድንበር ማቋረጥ የተለመደ ነው። የኤርትራ ጠረፍ ጠባቂዎች ህግ ወጥ ሸቀጦችን ከያዙ የሚወርሷቸው ሲሆን ከሳምንት ሳምንት ቁጥጥሩ እየጠበቀ መጥቷል።

የድንበር አካባቢ ፀጥታን በተመለከት የአስመራ መንግስት የፀጥታ ሰራተኞቹን በስውር በማስገባት የመንግስት ተቃዋሚ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን እስከማፈንና ከኤርትራ ተሰደው በኢትዮጵያ ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች በከፍተኛ ስጋት እንዲኖሩ ያደረገ ክስተት ተፈጥሯል። የኤርትራ መንግስት ይህን የሚያደርገው ከኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ አግኝቶ ስለመሆኑ አይታወቅም።

ከኤርትራ ወገን ያናገርናቸው ምንጮቻችን እንደነገሩን ባለፈው አንድ አመት በተለይም በቅርብ ሳምንታት የአስመራን መንግስት የሚቃወሙና በሀገሪቱ የስርዓት ለውጥ እንዲኖር የሚፈልጉ ኤርትራውያን “በቃ” የሚል መጠሪያ የሰጡትን የተቃውሞ ዘመቻ እያደረጉ ነው። በሱዳንና በኢትዮጵያ የነበሩት ህዝባዊ አመፆች ስኬት ኤርትራውያኑንም እንዳበረታታቸውና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የሚደረገው ተቃውሞ እየተጋጋመ መምጣቱን የአስመራ ምንጫችን ይናገራሉ።

ወረቀት በመበተን የተጀመረው ተቃውሞ አሁን አሁን ይፋዊ ተቃውሞ እስከማድረግ ደርሷል። ይህም የአስመራን መንግስት ስጋት ላይ ጥሎታል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በባህር ማዶ ያሉ የኤርትራ ተቃዋሚዎች የሚያስተባብሩት ይህ ተቃውሞ በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃንም ይደገፋል የሚል ጥርጣሬ አላቸው። ስለዚህም ድንበር መዝጋቱ የዚህ ስጋት አንዱ አፀፋ ነው።

ሌላው ድንበሩ ክፍት በተደረገ ወቅት በገፍ ወደ ኢትዮጵያ የኮበለሉ ኤርትራውያን ቁጥር ለኤርትራ ደህንነት ስጋትን የሚያጭር ሆኖ በመገኘቱ ፍልሰተኞቹን ለማቆም ድንበሩን መዝጋት አስፋልጓል ይላሉ የአስመራ ሰዎች።

እንዲህ ውስብስብ የፀጥታ ስጋት ውስጥ ያለችው ኤርትራ ሁለቱን አገሮች ወደ አንድ ማህበረሰብ ያሸጋግራል የተባለለትን ስምምነት በቶሎ ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነባትና ስምምነቶቹ ደረጃ በደረጃ እንዲታዩ እንደምትመርጥ እየገለፀች ነው።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከወራት በፊት ሁለቱን ሀገራት ወደ አንድ ማህበረሰብ የሚያመጣ ታሪካዊ ሰነድ አዘጋጅተናል ቢሉም አሁን አቋማቸውን ከልሰዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ማናቸውም ስምምነት ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት የአልጀርሱ ስምምነት ተተግብሮ የሁለቱ ሀገሮች ድንበር አንዲለይ በርካታ ኤርትራውያን ይፈልጋሉ። [ዝርዝር የዋዜማ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/Bc7pTrvQAk0