gmo-food1ኢትዮዽያ የልውጥ ህያዋን (GMO) በሀገሪቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ህጓን አላልታለች። የህጉ መሻሻል አደገኛና የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም የሚጎዳ ነው ይላሉ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች። መንግስት በለገሾች ተፅዕኖ ህጉን ለማሻሻል መገደዱን የሚያስረዱም አሉ።የፍሬስብሀት ስዩም ዘገባን አርጋው አሽኔ ያቀርበዋል

 

የባዮ ሴፍቲ ወይም የደኅንነት ሕይወት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ግንቦት ወር ፀድቋል። የአዋጁ መፅደቅ ለሀገሪቱ ስጋት ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ አዲስ በር ከፋች አድርገው የቆጠሩትም አሉ።
አብዛኛው ህዝቧ በገጠር የሚኖርና በእርሻ የሚታዳደረው ኢትዮዽያ ስለምን አዋጁን ማላላት ፈለገች የሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ ይፈልጋል።

አዋጁ የአካባቢ ተቆርቋሪዎችን ያስደነገጠ ሲሆን የአዋጁ መሻሻል የከፋ የጤና የአካባቢና የኢኮኖሚ ቀውሱ የካፋ ሊሆን ይችላል የሚለው ስጋት የብዙዎች ነው።

ቀደም ሲል በ2001 ዓ.ም. በጄኔቲክ ምሕንድስና (GMO) የተለወጠ ህያው ወደ ኢትዮጵያ በሚገባበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያስችል እጅግ ጥብቅ የተባለ የኢትዮጵያ የደኅንነት ሕይወት አዋጅ ፀድቆ ነበር፡፡

የዚህ አዋጅ መፅደቅ በወቅቱ ተከስቶ ለነበረ ድርቅ በጄኔቲክ ምሕንድስና የተለወጠ የስንዴ ዕርዳታ ወደ አገር እንዳይገባ የሚል ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል ፡፡

ይህ አዋጅ በጄኔቲክ ምሕንድስና የተለወጡ ዘሮች ወይም ህያዋን ለጥቅም እንዳይውሉ ይከልክል እንጂ ለምርምር፣ ለትምህርትና ለሙከራ በዝግ ላብራቶሪ መከናወን የሚቻልበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡

የ2001ዱ አዋጅ መቅድም የህጉ መውጣት አስፈላጊ የሆነበትን ጉዳይ ሲገልጽ ከልውጥ ሕያዋን ሊከተል ከሚችል ጠንቅ ህብረተሰቡን አካባቢውን እና ኢኮኖሚውን ለመጠበቅ መሆኑን ያመለክት ነበር፡፡ አላማውንም “በሰውና በእንስሳት ጤና፣ በብዝሐ ሕይወት፣ በአካባቢ፣ በማህበረሰቦችና በአጠቃላዩም በሀገር ላይ ከልውጥ ሕያዋን ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማስቀረት ወይም ቢያንስ እስከ ኢምንታዊ ደረጃ ድረስ ማሳነስ ነው” ሲል በግልጽ ያስቀምጥም ነበር፡፡

ነግር ግን በቅርቡ የተሸሻለው አዋጅ ድንጋጌ ክልካላዎቹን በመሻር የልውጠ ህያዋን ምርቶችን በቀላሉ ወደ አገር ውስት ለማስገባት በር የሚከፍት በመሆኑን የአካባቢ ጠቆርቋሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡

ህጉን ማሻሻል ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው የኢንዱስትሪው ልማት ለመደገፍ ሲሆን በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ማነቆ ተደርጎ የሚጠቀሰውን የግብአት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ያለመ ነው፡፡

በዚሁ ዘርፍም ልዩ ትኩረት የተሰጠው የጨርቃጨርቅ ንዑስ ዘርፍም ዋና ግብአት የሆነውን የጥጥ ምርት የሚታይበትን እጥረት በዘላቂንት ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ የቀረበው ደግሞ ቢ.ቲ ኮቶን ተብሎ የሚታወቀውንና በዘረ መል ምህንድስና የሚመረተውን ባይተዋር የጥጥ ምርት ለማስፋፋት ሲባል ነባሩን ህግ ማሻሻል ማስፈለጉን ተገልጿል፡፡

ነገር ግን የአካባቢ ተቆርቋሪዎች አሪቱ ካላት ያልተነካ ሰፊና ለም መሬት አንጻር ተፈጥሯዊን የጥጥ ምርት የኢንዱስትሪው ፍላጎት ለማሟዋላት የራስን አቅም መገንባት እየተቻለ በውጪ አገራት ኩባንያዎች ተጽዕኖ ጥብቅ የነበረውን አዋጅ ማላላት ሀገርን የሚጎዳ ውሳኔ ነው፣ ሳይንሳዊ መሰረትም የለውም ሲሉ መከራከሪያ ያቀርባሉ።

በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ በዘረ መል ምህንድስና ትልቅ ጡንቻ እንዳለው የሚነገርለት ሞሳንቶ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ማድረጉን በመጥቀስ የሚከራከሩም አሉ፡፡
ዘረ መል ውይም ልውጥ ህያዋን (Genetically Modified Organism-GMO) በሰለጠነው አልም ላሉ ኩባንያዎች በቀላሉ ጥገኛ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር ሀገር በቀል የሆኑ የብዝሃ ህይወት መሰረትን ያናጋል። የጤና ቀውሱም በአለም አቀፍ ደረጃ ስጋት እንደሆን ቆይቷል።

የኢትዮዽያ መንግስት አዋጅ አውጆ ህግ የማላላት ስራውን የሰራው በተለይ ከዩናይትድ ስቴትስ የልማት ድጋፍ ለማግኘትና የለጋሽ ሀገራቱን ለማስደሰት ነው የሚሉ ውስጥ አዋቂዎችም አሉ። በብዙ ታዳጊ ሀገሮች የልውጥ ህያዋንና ዘረመል ምህንድስና ጉዳይ ከሀገር ሉአላዊነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

የዘረ መል ምህንድስናን የሚደግፉ ምሁራን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢንደስትሪ የሚሆን ተረፈ ምርት ለማምረት ዘርፉ ሁነኛ አማራጭ ነው ይላሉ። ይሁንና ሳይንሱን በተግባር ለማዋል በቂ የሰውና የቴክኖሎጂ አቅም የሌላቸው ሀገራት ከጥቅሙ ጉዳት አመዝኖ ይታያል።