Eritrean Air Force attack plane
Eritrean Air Force attack plane

(ዋዜማ ራዲዮ)  ኢትዮዽያና ኤርትራ የተለመደውን የጦርነት ዛቻ ከሰሞኑ እንደ አዲስ ታያይዘውያል። በኤርትራ የአሰብ ወደብ የአረብ ሀገራት የጦር መርከቦች ከመስፈራቸው ጋር ተያይዞ አፍቃሪ ኢህአዴግ የሆኑ የመገናኛ ብዙሀን “መንግስት ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስጠብቅ” ሲሉ አስተያየት አስፍረዋል። በአሰብ የውጪ ሀይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንግዳ ባልሆነበት የጦርነት ዛቻን ምን አመጣው የኤርትራው ፕሬዝዳንት የኣአዲስ አመት ንግግርስ ስለሁኔታው ምን ይነግረናል?

ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች-አድምጡት

የኤርትራ ፕሬዚዳንት አሳይያስ አፈወርቂ በ2016 አዲስ ዓመት ዋዜማ ለዜጎቻቸው፣ ለኤርትራ መከላከያ ኃይል እና “የኤርትራ ወዳጆች”ላሏቸው አካላት የመልካም ምኞት መልዕክታቸው ነጻነታቸውን ሕልው ያደረጉ ኤርትራውያን አሁንም ሳይታክቱ በቁርጠኝነትመስዋዕትነት እንዲከፍሉ፣ ብሔራዊ ሉዓላዊነታቸውን በማስከበር ረገድም እንዲተጉ  የሃገሪቱ መጻኢ ጊዜ ብሩሕነትም በዚሁእንደሚመዘንና እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡

በዕድሜ የአፍሪካዋ ሁለተኛ ወጣት ሃገር ከሶስት ጎረቤቶቿ ማለትም ከየመን፣ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ጋር የድንበር ውዝግብ ውስጥ  ገብታ የነበረ ቢሆንም ከየመን ጋር አንጻራዊ ሠላም በማውረዷ፣ ከጂቡቲ ጋር የከፋ ደም መቃባት ውስጥ ያልገባች መሆኗ የፕሬዚዳንቱመልዕክት ለማን እንደተሰነዘረ ግልጽ ነው፡፡ ከሰሞኑ በሰፊው በኤርትራ ቲቪና ራዲዮ ከሚቀርበው የኢሳይያስ ዋና ቃለ ምልልስ በፊትየቀረበው የመልካም ምኞት መግለጫ ላይ የኤርትራ መከላከያ ኃይል በስም መጠቀሱም በራሱ የሚጠቁመው ነገር አለ፡፡

ከዚያ ወገን ከሚሰነዘረው በማይተናነስ መልኩ በዚህኛውም ወገን ተመሳሳይ ነገር እየቀረበ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝባለፈው ሰሞን የሰነዘሩት ዛቻና ማስፈራሪያ ለአገዛዙ ቅርበት ባላቸው ሚዲያዎች እየተራገ ነው፡፡ ኃይለማርያም በኤርትራ ወታደራዊእንቅስቃሴ ጀምረዋል የተባሉት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የማተራመስአጀንዳ ለማራመድ የሚሞክሩ ከሆነ መንግስታቸው እርምጃ እንደሚወስድ ለማሳሰብ አልሰነፉም፡፡ አንዳንድ ወደ ኢሕአዴግ ያዘመሙ ድረገጾችም ሳዑዲና ኤመሬትስን የሚያስደነግጥ ወታደራዊ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከመቼውም በተለየ እየቀረበ የሚገኘውን የኦሮሞ ማሕበረሰብ የመብት ጥያቄን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ ትዕዛዝ በርካታንጹሐን ዜጎች እየተገደሉ ባለበት በዚህ ወቅት የኢሕአዴግ መንግስት በኤርትራ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ እየቀረበ ያለውንጥያቄ “አቅጣጫ ከማስቀየስ ያላለፈ አጀንዳ” የሚሉት ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ይሕ ሰሞናዊ አጀንዳ የድረ ገጾች ብቻ ሳይሆን በኢሕአዴግበራሱ የተቀነባበረ ነው የሚሉት እነዚሁ ወገኖች ሟቹም ሆኑ ሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማ ሲቀርቡ፣ በምርጫ ሰሞን፣በግንቦት 20  አለያም ወቅታዊ ትኩሳት በሃገሪቱ በተከሰተ ወቅት ሁሉ በሻዕቢያ ላይ እርግማንና ዛቻ ሲያወርዱ የነበረው አጀንዳበማስቀየር የተለመደ አሰራራቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ ፡፡ የሰሞኑንም መግለጫ ከዚሁ ጋር ይፈርጁታል፡፡

ኢትዮጵያ እና እርትራበ “ሠላምም ጦርነትም የለም” ሁኔታ እንዲዘልቁ ሩብ ክፍለ ዘመን ሥልጣን ላይ የቆዩት  የሻዕቢያ እና የኢሕአዴግ ፍላጎታቸው መሆኑን ይነገራል ፡፡ ለሥልጣን ማራዘሚያ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሙበታል፡፡

ስራቴጂካዊነቷ አሰብ ከወደብ አልባዋ ባለ 100 ሚሊየን ሕዝብ ኢትዮጵያ በ161 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብትገኝም አሁን በአሰብ ላይወታደራዊ እርምጃ ይወሰድ ለሚሉ ኢሕአዴጋውያን አሳሳቢ የሆነችበት ወቅት አልነበረም፡፡ የአሰብ ወደብ የአረብ ሃገራት ባሕር ኃይልመናኸሪያነት ከሰሞኑ ተጋጋለ እንጂ የኤርትራ ወደቦች የተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሳይለያቸው ነው የቆየው፤ ባለ አነስተኛሕዝብና የደከመ ኢኮኖሚ ባለቤት ትንሹዋ ሃገር በሚሊየን ዶላሮች የምታገኝባቸው ደሴትና ወደቦቿን እንደ እስራኤልና ኢራን ያሉባላንጣዎች በተመሳሳይ ወቅት የሰጠችበት ጊዜም ነበር፡፡ አሰብም ሆነ ቀይ ባሕርና ሌሎች ወደቦች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርእንዳሉት የግመል ውሃ መጠጫ ሳይሆኑ የኤርትራ ሕልውና ጭምር ሆነዋል፡፡ የወደብ ባለቤትነት አንዱ ጥቅምም ይሕ ነው፡፡

አሸባሪዎችን በመርዳት መረጃዎች የቀረቡባት፣ በዚህም የማዕቀብ “ዱላ” ያረፈባት ኤርትራ ከምዕራባውያን ጋር ደጋግማ ዓይንና ናጫብትሆንም ከመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሃገራት ጋር ግን የጠነከረ ወዳጅነት አላት፡፡ የአረብ ሊግ የታዛቢነት ወንበርም አላት፡፡ ከኢራን፣ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያና ግብጽ ጋርም የተለየ ወዳጅነት  አላት፡፡ ኢራን ለየመን ሁቲ አማጽያን የጦር መሳሪያ ስታቀብልና ሥልጠና ስትሰጥየቆየችው በኤርትራ ግዛቶች እየተሸጋገረች ነበር፡፡ በሶቪየት ሕብረት የተገነባውን የአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ለማደስ በሚል ሰበብ ኢራንከስድስት ዓመት በፊት በወደቡ አቅራቢያ ወታደሮችን ማስፈር በመቻሏ ኤርትራ በእጅጉ ተጠቃሚ ነበረች፡፡

ለአብነት ያሕል በ2009ኤርትራ የኢራንን የኒውክሊየር ፕሮግራም በአደባባይ እደግፋለሁ በማለቷ ብቻ ከኢራን ኤክስፖርት ዲቨሎፕመንት ባንክ 35 ሚሊየንየአሜሪካ ዶላር ነበር የተበረከተላት፡፡ እስራኤልም በዳሕላክ ደሴቶች የደሕነነትና የቁጥጥር ሠፈር የኖራት በዚያው ተመሳሳይ ወቅትነበር፡፡ ለዚህም ነው የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የጦርና የደሕንነት ሠፈር በኤርትራ መኖር አዲስ ባልሆነበት ሁኔታ ኢሕአዴግኤርትራ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ይውሰድ የሚለው ፕሮፓጋንዳ ከጀንዳ ማስቀሻነት ያለፈ አይደለም የሚል ትችት እየቀረበበት ያለው፡፡

እርግጥ ነው ዓለም አቀፉ የጂኦ ፖለቲካና ኢንተለጀንስ ተቋም ከወራት በፊት ባሰራጨው መረጃ በኤርትራ ሄሊኮፕተር ጭምርየሚያሳርፉ የጥምረቱ ኃይል የሆኑ ሶስት የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ሃገራት ባሕር ኃይል መርከቦች እንደሚገኙባት አረጋግጧል፡፡ ከሱዳንወታደሮች ጋርም የኤርትራ ጦር የመን ከዘመተው ኃይል ጋር መሰማራቱን የሚገልጹ ምንጮችም አልታጡም፡፡ የጦር ሠፈር መመስረቱንየሚያረጋግጥ ዜና ማግኘት ባይቻልም፡፡

ኢሕአዴጋውያን “ሌጋሲያቸውን እናስቀጥልላቸዋለን” የሚሏቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትከመጀመሩ ጥቂት ወራት በፊት በጅማ ከተማ ተካሂዶ በነበረው የፓርቲያቸው ኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ “በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር የጥይትድምጽ የለም፤ የጥይት ድምጽ የሚሰማው በነፍጠኞች ልብ ውስጥ ነው” የሚል የተዓብዮ ገለጻ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የዛሬአራት ዓመት በማርች 2011 ዓ.ም ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዘናዊ በኤርትራ ጉዳይ የያዙትን ፖሊሲ መቀየራቸውን ባሳወቁበትማብራሪያ  “የኤርትራ ፖሊሲ ወይ ደግሞ መንግስት እንዲቀየር እንሰራለን፤ ይሕን የምናደርገው በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ አለያም በሌላመንገድ ሊሆን ይችላል” ነበር ያሉት፡፡ እሳቸው ይሕን ይበሉ እንጂ ከጦርነቱ ወዲህ ኤርትራን በተመለከተ የኢሕአዴግ መንገድ እምብዛምለውጥ አልታየበትም፡፡

ለወትሮው ከአዲስ አበባዎቹ ግዮንና ዋቢ ሸበሌ ሆቴል የማይጠፉት ወጪያቸው ከኢትዮጵያ ካዝና ሲሸንላቸው የቆዩት የሻዕቢያተቃዋሚዎች በኢሕአዴግ ተስፋ በመቁረጥ ይመስላል ከሰሞኑ ካሉበት በመጠኑ ራቅ ብለው በኬንያ ለመሰብሰብ የመረጡት፡፡