ዋዜማ ራዲዮ- CUD leadersገዥው ግንባር ኢህአዴግ አስገዳጅ የፖለቲካ ቀውስ ሲገጥመው ድርድርና የፖለቲካ ማሻሻያ አደርጋለሁ፣ ከሰማይ በታች የማልደራደርበት ጉዳይ አይኖርም ሲል ይደመጣል። በተግባር ግን ግንባሩ በታሪኩ ቃሉን የመጠበቅም ሆነ ህዝብን የማክበር ድፍረት የሚያንሰው አስመሳይ ነው የሚሉት ብዙዎች ናቸው። ለዚህም ይመስላል እንደሰሞኑ እስረኞችን እፈታለሁ፣ ማዕከላዊን እዘጋለሁ፣ ታድሼ ችግሮቼን ፈትቻለሁ ሲል አብዛኛው ማህበረስብ በጥርጣሬ የሚመለከተው። ተከታዩ ዘገባ ኢህአዴግ የፖለቲካ ክህደት የፈፀመባቸውን ክስተቶች የኋላ ታሪክ እየጠቀሰ የሚነግረን ቻላቸው ታደሰ ነው።

[ይህንና ተያያዥ ጉዳዮችን ከግርጌ በድምፅ መስማት ይችላሉ]

በፖለቲካዊ ቀውስ እየተናጠ ያለው የገዥው ግንባር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያካሄደውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ በመግለጽ ዐለም ዐቀፍ ትኩረት የሳበ ሆኖም ግን ግልጽነት ርስበርሱ የሚጣረስ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫው የጠራ መልዕክት የሌለው መሆኑ ደሞ በገዥው ግንባር ውስጥ ወይም በመንግስት ተቋማት መካከል ያልረገበውን ፍትጊያ እና አንድ ሀገራዊ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል ማዕከላዊ አካል እየጠፋ ስለመሄዱ ጠቋሚ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ሳምንታት በፈጁ ስብሰባዎች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ያልቻለው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እና የሚመራው መንግስት የገለልተኛ አካላትን ጣልቃ ገብነት የሚፈልጉበት ሁነኛ ሰዓት የደረሰ ይመስላል፡፡

በርግጥ በግትርነቱ የሚታወቀው ኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ለመውሰድ ቃል ሲገባ ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ወደ ተግባራዊነቱ ሲመጣ ግን ወገቤን ሲል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ወገኖች የሰሞኑን ቃል ኪዳኑን የሕዝብ ግንኙነት ብልጣብልጥት እንጂ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ሲል የወሰደው ልባዊ ርምጃ አድርገው ለመቁጠር የሚቸገሩት፡፡

ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ከተዘረጋ ወዲህ መንግስት የገባቸውን በርካታ ቃል ኪዳኖች በሕገ መንግስታዊም ሆነ በፖለቲካዊ መንገድ ማክበር ሳይችል ነው ሀገሪቱ ላሁኑ ፖለቲካዊ ቀውስ የተዳረገችው፡፡ ለአንዳንዶቹ ቃል ኪዳኖቹ እንዲያውም ገዥው ፓርቲ ጭራሹን ተቃራኒ አቅጣጫ በመከተሉ የሀገሪቱን ቀውስ ራሱ አባብሶታል፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዐመታት ወጣቱ ትውልድ “በትናንት” እና “ዛሬ” ላይ ብቻ የሚያጠነጥነውን የድርጅቱን ትርክት ወደ ጎን በመግፋት “የእኛ እና የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምንድን ነው?” የሚል ወደፊት ብቻ የሚመለከት ጥያቄ ያነሳው ኢሕአዴግ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ መሆኑ ድርጅቱን ውጥረት ውስጥ ነው የከተተው፡፡ ዳሩ ለመብት ጠያቂ ወጣቶች ሁነኛ አመራር የሚሰጥ የተደራጀ አካል አለመኖሩን እንደ ጥሩ እድል በመቁጠር በመዘናጋቱ ገፍቶበታል፡፡

እዚህ ላይ ገዥውን ድርጅት ወደዚህ አጣብቂኝ ያስገቡት የራሱ ውስጣዊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህን ለመረዳት እንግዲህ ግንባሩን ከሦስት መስኮች ማለትም ከታሪካዊ አመጣጡ፣ ከድርጅታዊ አወቃቀሩ እና ከውስጣዊ ባህሉ አንጻር ማየት ነው ጠቃሚ የሚሆነው፡፡

ገዥው ድርጅት መንግስት ሲመራ የኖረው ከቅድመ-1983 በፊት ከነበረው የጦር ሜዳ ውጊያ ስነ ልቦናው ሳይላቀቅ ነው፡፡ ፖለቲካው ሁሉ የአጥቂነት ወይም ተከላካይነት ስነ ልቦና የተላበሰ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ በተለይ ለ17 ዐመታት በጦር ሜዳ ተዋግቶ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ጦር ሠራዊት ማሸነፍ መቻሉ የፈጠረበትን ስነ ልቦና በቀጥታ ወደ መንግስታዊ አመራሩ ስላጋባው አዳዲስ እና ነባራዊ ፖለቲካዊ ቅሬታዎችን ባግባቡ እንዳያስተናግድ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡

የኦነግ መባረር

ኢሕአዴግ ገና በጧቱ በ1992 ዓ.ም ነበር ዋነኛውን ተቃዋሚውን እና የሽግግር መንግስቱ መስራች የነበረውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግን በፖለቲካዊ ጫና ከሂደቱ ገፍቶ ያስወጣው፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተትም በመድበለ- ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ የፈጸመው የመጀመሪያ ጉልህ የፖለቲካ ሃጢያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የኦነግ ፖለቲካዊ ቁመና ምንም ይሁን ምን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ውስጥ ውክልና አጥተው ድምጽ አልባ ሆነው የቀሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ከዚያም ሊያከብረው ምሎ የተገዘተለትን እና ሥልጣን ከነጻ እና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሳትን ብቻ እንዲገኝ ለማድረግ የገባውን ሕገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን በ1997ቱ መናዱ ሌላው አሉታዊ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ምርጫው የከፈተውን ዴሞክራሲያዊ ምህዳር እና ምህዳሩም የፈነጠቀውን ሁለንተናዊ ተስፋ ወዲያውኑ መልሶ ለማጨለም ገዥው ድርጅት ያለ የሌለ ሃይሉን ነው የተጠቀመው፡፡ የምርጫውን ውዝግብ ተከትሎ የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽ በሃይል መደፍጠጥ መቻሉንም እንደ ጥንካሬ እንጂ ውሎ አድሮ ሀገራዊ መዘዝ የሚያመጣ ፖለቲካዊ ችግር አድርጎ ለማየት ፍላጎቱ አልነበረውም፡፡ ምንም እንኳ በምዕራባዊያን ወዳጆቹ ጫና በምርጫው ቀውስ ሰበብ ያሰራቸውን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟገቾች ዘግይቶ በይቅርታ ቢፈታም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን ከሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማት ይልቅ ዋነኛ መተማመኛውን በጸጥታ መዋቅሩ ላይ ብቻ በማድረግ ነበር በአፋኝ አዋጆች እና ሌሎች ፖለቲካዊ አሰራሮች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የዴሞክራሲ መፈናፈኛ ክፍተቶችን ሁሉ ጠርቅሞ የዘጋው እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ጠንክሮ የገፋበት፡፡

በ2007ቱ ብሄራዊ ምርጫ “መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ” በማለት የተቃዋሚ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ጨዋታው ማግለሉ ደሞ በሕገ መንግስታዊ እና በፖለቲካዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ለማስፋት በገባው ቃል ኪዳን ላይ በረዶ የቸለሰ ነበር፡፡

ላለፉት ሁለት ዐመታት የዘለቀውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ባለፈው ዐመት መባቻ ላይ መንግስት መሠረታዊ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ቢሆንም ከጥቃቅን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እያደረገ ካለው የይስሙላ ድርድር በስተቀር ሁነኛ መሻሻል ሳያደርግ እነሆ ዐመት ከመንፈቅ ሞልቶታል፡፡ ገና ያልተፈጸመው የሰሞኑ ቃል ኪዳንም ድንገተኛ እንጂ የአምናው ቃል ኪዳኑ ውጤት እንዳልሆነ ቀደም ሲል ያወጣቸው መግለጫዎች ምስክር ናቸው፡፡

“ለሀገራዊ መግባባት እና ዲሞክራሲን ለማስፋት ስል የፖለቲካ እስኞችን እፈታለሁ” ለማለቱ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ገፊ ምክንያቶች መካከል ያልረገበው ሕዝባዊ አመጽ፣ ብሄረሰባዊ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መባባስ እና በገዥው ግንባር ውስጥ ያለው መገፋፋት ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ድርጅቱ ለዚህ ውሳኔ የበቃው ውስጣዊ የሃይል ሚዛኑ በመናጋቱ ወይም መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረጉ ስለመሆኑ ግን በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡ በተለይ በፓርቲው ውስጥ ስላለው የሃይል ሚዛን መፈታተሸ ከመላ ምት በስተቀር በትክክል እስከምን ድረስ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡

ከአንገት በላይ ድርድር

ኢሕአዴግ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከሀገር ዐቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እንዲደራደር ወይም ለብሄራዊ እርቅ በሩን እንዲከፍት ሲጠየቅ “የፖለቲካ መስመር ልዩነት እንጂ የተጣላ አካል የለም፤ ማን ከማን ነው የሚታረቀው?” ከሚለው አቋሙ ፈቀቅ አላለም፡፡ ለድርድር ፖለቲካዊ ፍቃደኝነት ባሳየባቸው አጋጣሚዎች እና ለድርድር በተቀመጠባቸው አጋጣሚዎችም ቢሆን በአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ጥቅም እና የሕዝብ ግንኙነት ትርፍ ላይ ብቻ ሲያተኩር እንጂ በቅንነት ስለማይገባበት ራሱን ተጠያቂ ከማድረግ አልፎ ሥልጣን የማጋራት ፍንጭ እንኳ ለማሳየት አልደፈረም፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት በሀገር ደረጃ ዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ እና ለብዝሃ አስተሳሰብ ሆደ ሰፊ መሆን ተስኖት ከሃያ ዐመታት በላይ ጥቃቅን ተቃናቃኞቹን ሳይቀር በወህኒ ቤት ሲያጉር እና ለስደት ሲዳርግ የኖረው፡፡ “በፖለቲካዊ ማሻሻያ ስም የምከፍተው ቀዳዳ ሊቀለበስ በማይችል የነጻነት ጠያቂዎች ማዕበል ቢያጥለቀልቀኝስ?” የሚል ስጋት ሰንጎ እንደያዘው የሚያጠራጥር የማይሆነው ለዚህ ነው፡፡

የሰሞኑ የገዥው ግንባር መግለጫ “ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና ዲሞክራሲውን ለማስፋት” እንደሚፈልግ መግለጹ ወትሮውንም ቢሆን “ሀገራዊ መግባባት መፍጠር” እና “ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን የማስፋት” ጉዳዮች የተከዱ ቃል ኪዳኖች ስለሆኑ ነው፡፡

ሌላኛው አጣብቂኝ ውስጥ የከከተተው ደሞ ዋዜማ ደጋግማ ያነሳችው ግንባሩ ከብሄር ተኮር አወቃቀሩ ያለመላቀቁ ነገር ነው፡፡ አሁን ያለው አወቃቀሩ ብዝሃነትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ አንድነት ወይም አንድ የጋራ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ አስተጓጉሎታል፡፡ በውስጡ ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ በዋነኛነት የብሄረሰብ ማንነትን መሠረት ያደረገው ውስጣዊ ፖለቲካው ውሎ አድሮ ድርጅታዊ ሽኩቻ እና ብሄር ግጭት አስከትሏል፡፡ አሁን እየለፈፈለት ያለው ዲሞክራሲንም የማስፋት ጉዳይም ማነቆ የገጠመው የብር-ተኮር ፖለቲካው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የመደፍጠጥ ባህሪ ስላለው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የግንባሩ የሰሞኑ መግለጫ ይህንኑ ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳየ ቢመስልም ስለ መፍትሄው ግን ፍንጭ አልሰጠም፡፡

ገዥው ግንባር ስለ ውስጣዊ ዴሞክራሲው ደጋግሞ ቢሰብክም ለመንግስታዊ ሥራው ሊመነዝረው ይቅርና ለራሱ ለአባላቱ እንኳ የሚተርፍ እንዳልሆነ የሰሞኑ መግለጫ ብቻ በቂ አብነት ይሆናል፡፡ በመሠረቱ የኢሕአዴግ ዋነኛ ችግር በብሄራዊ አባል ድርጅቶቹ መካከል የአግድሞሽ የርስበርስ ግንኙነት አለመዳበሩ እንደሆነ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በብአዴን እና ኦሕዴድ መካከል የበይነ-ድርጅት ዴሞክራሲያዊ ግንኙነቶች ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ ግን ከሞላ ጎደል በሕወሃት የሚዘወረው ማዕከላዊው ግንባሩ ባጭሪ ሊቀጫቸው በማሰብ የበይነ-ድርጅት ያልተገባ ቡድናዊ ጉድኝት ስለፈጠረው አደጋ ሰባኪ ሆኖ ብቅ ማለቱ የውስጣዊ ዴሞክራሲ ባህል ነገር ባዶ ትርክት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ይልቁንስ ከሰሞኑ ውሳኔው በተቃራኒ በነባሩ ውስጣዊ ድርጅታዊ ባህሉ እንደሚመካ እና “ዴሞክራሲያዊ ማዕላዊነት” የሚባለውን ገዥ መርሁንም በበለጠ እንደሚያጠብቅ ነው መግለጫው ግልጽ ያደረገው፡፡

የታሪክ ዕዳ

ባጠቃላይ ገዥው ድርጅት ቀውስ ውስጥ የገባች ሀገር ይዞም እንኳ ታሪካዊ አመጣጡ በፈጠረበት ስነ ልቦና፣ በድርጅታዊ አወቃቀሩ እና በውስጣዊ ድርጅታዊ ባህሉ ረገድ የረባ መሻሻል ማድረግ አልቻለም ወይም አልፈለገም፡፡ የሰሞኑ መግለጫው አላማም ሀገራዊ ቀውስን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ በብሄራዊ አባል ድርጅቶች መካከል የሃሳብ እና የተግባር አንድነት መረጋገጡን እና ድርጅታዊ ቁመናቸው አሁንም ያልተዳከመ መሆኑን ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ለመግለጽ የታለመ ነው የሚመስለው፡፡ ለዚህም ነው ገለልተኛ የሆነ አደራዳሪ ወይም ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ ነዳፊ አካል ጣልቃ ካልገባ በስተቀር ዋነኛው የችግሩ ምንጭ የሆነው ኢሕአዴግ ዘላቂ መፍትሄ የማምጣት እድሉ የተመናነ መሆኑን ብዙ ታዛቢዎች የሚያሳስቡት፡፡

በርግጥ ሀገሪቱ በሰላም፣ ግጭት አፈታት እና አደራዳሪነት ረገድ እሴቶችን ያካበቱ ሀገር ዐቀፍ እና ተቋማዊ ቁመና ያላቸው ተቋማት የሌሏት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዳዴ በማለት ላይ የነበሩትን ሀገር በቀል እና የውጭ ሲቪል ማህበራትንም በሥራ ላይ ያለው አፋኝ አዋጅ አዳክሟቸዋል ወይም ጨርሶ ያጠፋቸው መሆኑ ግን ከባድ መሰናክል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በጎረቤት ኬንያ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይሎችን በማስታረቅ ሁነኛ ሚና የምትጫወተው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከወራት በፊት ስለ ሀገራዊ ቀውስ መፍታት እና ሀገር ዐቀፍ ድርድር ማድረግ አስፈላጊነት ጀምራው የነበረው ጥረት ምክንያቱ ሳይታወቅ ብዙም ሳይጓዝ ነው ተዳፍኖ የቀረው፡፡ ያም ሆኖ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የኢሕአዴግን ይሁንታ ሳይጠብቁ እና ድርጅቱ ለሚመራው መንግስት የማርያም በር ሊሰጥ በሚችል መልኩ ሰሞኑን የሲቪል ማህበራትን ምህዳር ለማስፋት ቃል መገባቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ አጣዳፊ ግዴታቸው አድርገው ቢወስዱት አንድ ተስፋ ሰጭ ርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡

ላሁኑ ውስብስብ ሀገራዊ ቀውስ በምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች ጥረት ላይ ብቻ የሚመኩ ወገኖች ግን ፈጠን ብለው ሀገር በቀል መፍትሄ አመንጪ ገለልተኛ አካላትን ወደመፍጠር ፊታቸውን ማዞር ያለባቸው ወቅት የደረሰ ይመስላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ላሁኑ ቀውስ መነሻ የሆነው በ1983 ዓ.ም አደራዳሪ የነበሩት የአሜሪካው ዲፕሎማት ሔርማን ኮኸን ወታደራዊ ድል ያገኘው ኢሕአዴግ የሀገሪቱን እጣ ፋንታ በዋነኛነት ብቻውን እንዲወስን እድል መስጠታቸው መሆኑ መዘንጋት የለበም፡፡

የሰላም እና ቀውስ መውጫ ሃሳቦችን ለሚያመነጩ ገለልተኛ አካላት ችግር የሚፈጥርባቸው ሌላው ጉዳይ የመንግስት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በገዥው ፓርቲ መዋቅር የተዋጡ መሆናቸው እና የትኛውን መንግስታዊ አካል ማናገር እንዳለባቸው ግልጽ ያለመሆኑ ነገር ነው፡፡ ችግሩ የመንግስት እና ፓርቲ መዋቅር በመቀላቀሉ የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ለራሳቸው የሥልጣን ማዕከል እየሆኑ መምጣታቸው የመንግስት ማዕከላዊ አመራር የቱ ጋ እንደሆነ ግራ እያጋባ መምጣቱ ጭምር ነው፡፡

ሰሞኑን የኢሕአዴግ “የእስረኞችን እፈታለሁ” ቃል ኪዳን በራሱ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ምዕራፍ ሊከፍት ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ እና ፓርቲው የሚመራው መንግስት ቁመና ግን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ምዕራፍ እውን ሊያደርግ ይቅርና ራሱ ድርጅቱ፣ መንግስት እና ሀገሪቱ እየገቡበት ያለውን ውጥንቅጥ ችግር ገና ባግባቡ የተረዳው አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ መግለጫው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በጎ ርምጃ ተደርጎ ቢወሰድለትም ለድርጅቱም ሆነ ለመንግስት የወደፊት አካሄድ መሠረት የጣለው ግን ከሳምንት በፊት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያወጣው እና ጠበቅ ያለ የተማከለ አመራርን እንደሚከተል የገለጸበት መግለጫ እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ድርጅቱ የሀገሪቱን ቀውስ በቅጡ ተረድቶት ዲሞክራሲያዊ ምዕራፍ ለመክፈት ፍቃደኝነት ቢያሳይም እንኳ የመንግስት ሥልጣን ስለያዘ ብቻ ብቻውን የሚወጣው የቤት ሥራ የመሆኑ ነገር ያከተመ ይመስላል፡፡ ይህንና ተያያዥ ጉዳዮችን ከግርጌ በድምፅ መስማት ይችላሉ

https://youtu.be/P1rP-f7W2e8