girum at stageሀሳብን በነፃነት መግለፅ ፈተና በሆነባት ኢትዮዽያ ዛሬ ዛሬ አማራጭ የመተንፈሻ መንገዶች መፈለጉ የግድ ይመስላል። ከአመታት በፊት የተጀመረው ጦቢያ ግጥምን በጃዝ ውርሀዊ መሰናዶ ለአዲስ አበቤዎች ተናፋቂና ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግድፈቶች የሚተቹበት፣ የጥበብ አድባር የምትነግስበት እየሆነ ነው ይለናል የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን …..እስቲ አድምጡት

To learn More about Tobia Poetic Jazz CLICK the links Meron Getnet    Eyayu Fungus

በመሃል አዲስ አበባ ገጣምያን፤ ወግ ፀሃፍያን እና ዲስኩር ነጋሪዎች በሰላ ብእራቸው የከተቧቸውን ፅሁፎቻቸውን ኢትዮጵያዊ ለዛ ካለው የጃዝ ሙዚቃ ጋር አዋህደው ወቅቱን በጉጉት ከሚጠብቁት አድናቂዎቻቸው ጋር ዘወትር ወር በገባ በመጀመርያው እሮብ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ በመገናኘት የጥበብ ፍቅራቸውን ይወጣሉ፡፡ የፕሮግራሙ አድናቂዎች ጥበብ የሰውን ልጅ በስሜት ሰቅዞ ሲይዝ ለማየት ትክክለኛው ቦታ ነው ይሉታል በመንቶ ስነጥበባት እየተሰናዳ የሚቀርበውን የ ጦቢያን ግጥምን በጃዝ ወርሃዊ ፕሮግራም፡፡ በእርግጥም እድል ገጥሞት በፕሮግራሙ ላይ ለታደመ ሰው ከአገራዊ አልባሳት ጀምሮ በመድረኩ የሚቀርቡት ግጥሞች፤ መነባንቦች፤ኮርኳሪ ሃሳቦችና አዝናኝ ዲስኩሮች ታዳሚያንን ሲያስቁ፤በተመስጥኦ በሃሳብ ባህር ላይ ሲጥሉ፤ ሲያስቆዝሙ፤ ሲያስቆጩ፤ ከፍ ሲልም ታዳምያንን በስሜት ከወንበር ሲያስነሱ ሊመለከት ይችላል፡፡ ከጃዝ ሙዚቃ ጋር ተዋህዶ፤ በጥበብ ስሜት ግሎ፤ በመድረኩ የሚነግሱ ገጣሚያንን ይዞ ከታዳሚያን ጋር የሚገናኘው ወርሃዊው የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም በእርግጥም በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ውስጥ ብቅ ያለ አዲስ ክስተት ይመስላል፡፡
በታህሳስ ወር 2001 ዓ.ም ላይ በወቅቱ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ተመርቀው በወጡ ወጣት ሙዚቀኞች ከተቋቋመው ሃራ ሳውንድ ባንድ ጋር በመሆን ግጥምን ከጃዝ ሙዚቃ በማዋሃድ ለመድረክ ለማቅረብ መመካከራቸውን የፕሮግራሙ መስራችና አባል ሰዓሊ እና ገጣሚ ምህረት ከበደ ታስታውሳለች፡፡ “ፕሮግራሙ ሲፀነስ ለብቻዬ ከሃራ ሳውንድ ጋር በመሆን ግጥም እንዳቀርብ ነበር፡፡” የምትለው ምህረት ነገር ግን በወቅቱ ሌሎች ጓደኞቻችንን ጨምረን ሰፋ አድርጎ የመስራት ሐሳብ ቀርቦ ተቀባይነት በማግኘቱ አበባው መላኩ፤ምስራቅ ተፈራ፤ ፍሬዘር አድማሱ፤ደምሰው መርሻ እና ዶ/ር ፍቃደ አዘዘን ጨምሮ በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ግጥምን በጃዝ ለመጀመርያ ግዜ በኮንሰረት መልክ መቅረቡን” ታስታውሳለች፡፡

Tobia poetic jazz
በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማሰረፍ እና ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት ባደረባቸው ገጣምያን የተጀመረው ግጥምን በጃዝ ሙዚቃ አዋህዶ የማቅረቡ ስራ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች መደበኛ ባልሆነ መልኩ ሲቀርብ ቆይቶ ከአራት አመት በፊት በሸበሌ ሆቴል ለአንድ አመት በየወሩ በተከታታይ ከቀረበ በኃላ ላለፉት ሶስት አመታት እየታየ ወዳለበት ራስ ሆቴል መዘዋወሩን ገጣሚያኑ ያስረዳሉ፡፡
ቋሚ ወንበር ያላቸው ከመቶ በላይ ታዳምያን በፕሮግራሙ አዘጋጆች አጠራር “የቤተሰብ አባላት”ን ጨምሮ በየመድረኩ በአማካኝ ከ1200 ሰው በላይ በየወሩ የሚታደምበትን ይህን ፕሮግራም ከሌሎች ብቅ ጥልቅ ከሚሉ መሰል ጅምር ፕሮግራሞች ምን ቢለየው ነው ተወዳጅነቱን ጠብቆ ሊዘልቅ የቻለው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በተወሰኑ ሆቴሎች ግጥምን በሙዚቃ አዋህዶ የማቅረቡ ጥረት እየተጀመረ በአጭር ቆይታ ሲከስም የራስ ሆቴሉ የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም እንደተወደደ የዘለቀበት ብዙ ምክንያት እንዳለው የፕሮግራሙ የረጅም ጊዜ ተከታታዮች ይናገራሉ፡፡ አስተያያተቸውን የሰጡን የፕሮግራሙ የረጅም ጊዜ ታዳሚዎች እንደሚያምኑት የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም እንደሌሎች ፕሮግራሞች ሳይቋረጥ በተከታታይ ለረጅም ጊዜ መቅረቡ፤ በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ውስጥ አንቱ የተባሉ ፀሃፍያንን ማሳተፉ፤ የሚደጋገሙ ፅሁፎች አለመብዛታቸው፤ ባብዛኛው በማህበራዊ ችግሮቻችን ላይ ውይይት የሚጭሩ ሃሳቦች መነሳታቸው እና ከግጥም በተጨማሪ መንፈስን የሚገዙ ኮርኳሪ መነባንቦችና ዲስኩሮች መቅረባቸው ለተወዳጅነቱ ጉልህ ሚና አበርክቷል ይላሉ፡፡ እንደ ሰዓሊ እና ገጣሚ ምህረት አተያይ የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም ጥራቱን እና ተወዳጅነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ለሚቀርቡት ፅሁፎች ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉ፤ዘውትር አዳዲስ ነገሮች መካተታቸው እና ሁሌም መድረኩን የሚመጥኑ ስራዎች እዲቀርቡ መትጋታቸው ለፕሮግራሙ መወደድ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ታስረዳለች፡፡
ያለፉትን አስራ አራት ተከታታይ ፕሮግራሞችን በቋሚነት መታደሟን የምትገልፀው የሂሳብ ባለሞያዋ ወጣት ህሊና የጦቢያን ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም ሁሌም በጉጉት እንደምትጠብቀው ትገልፃለች፡፡ ህሊና ከመዝናናት ባለፈ በመድረኩ የሚነሱት ማህበረሰባዊ ሂሶች እንደቀልድ ያለፈቻቸውን የጋራ ጉዳዮቻችንን መለስ ብላ እንድታያቸው እንደሚያደርጉዋትም ትናገራለች፡፡ በሌሎች መድረኮች የማታይታዩ ደፋር ሂሶች በዚህ መድረክ ላይ በስነጽሑፋዊ ለዛ እየታሸ መቅረቡም ለህሊና ርካታን ሰጥቷታል፡፡ በባህል ታጥረን ያልተነጋገርንባቸውን ማህበራዊ ችግሮቻችንን ከመድረኩ በግጥም ወይም በወግ መልክ ሲቀርብ ስትመለከትም ስነጽሑፍ ምን ያህል አቅም እንዳለው እንደሚያሳይ ትናገራለች፡፡ ለማሳያነትም እያዩ ፈንገስ የሚያቀርበውን ትጠቅሳለች፡፡ እያዩ ፈንገስ በማህበረሰቡ ውስጥ በቸልታ ወይም በፍርሃት ያልተነገሩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን እንደቀልድ እያሳቀ ለህብረተሰቡም ለሚመለከተውም አካል መቅረቡ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደሚረዳ ተስፋም ታደርጋለች ወጣቷ ህሊና፡፡
በርግጥ በዚህ ወርሃዊ ፕሮግራም ላይ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች ጭምር መነጋገርያ ሆነው ያለፉ በርከት ያሉ የጥበብ ስራዎች መቅረባቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡ በሃገራዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚቀርቡ የጥበብ ስራዎች በይበልጥ በመድረኩ ላይ ተቀባይነት ሲያገኙ መመልከታቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የፕሮግራሙ የረጅም ጊዜ ተከታታይ የኾነው የምህንድስና ባለሞያው ሃይሉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ላይ የሚቀርቡ ሂሶችና ስላቆች ወደፕሮግራሙ እንዲመጣ ከሚያደርጉት ዋነኛ ምክንያቶች መኾናቸውን ይመሰክራል ፡፡ ስለዲሞክራሲ፤ ስለኢኮኖሚያዊ ችግሮች፤ስለስደት እና በመሰል ጉዳዮች የሚቀርቡ ግጥሞች ፤ ወጎች እና ዲስኩሮች ከመድረኩ አለፎ በማህበራዊ ሚድያው መነጋገርያ ለመሆን የበቁበትም ምክንያት ለሃይሉ እነዲህ ያሉ ጉዳዮችን በግልጽ መነጋገር ባለመለመዱ ምክንያት ይመስለዋል፡፡ ትለቅ የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ኾኖ የከረመውንም የሚሮን ጊትነትን ግጥምም እንደምሳሊ ያነሳል፡፡
የፕሮግራሙ መስራች ገጣሚ እና ሰዓሊ ምህረት በመድረኩ በተቻለ መልኩ የተሻለ ስራ ለማቅረብ እንደሚጣር እና የተለያዩ በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያገኙ ግለሰቦችን በመጋበዝ ዲስኩር እንዲያቀርቡ ማድረጋቸውን ትናገራለች፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አያሌ ምሑራንን፤ታላለቅ የመድረክ ሰዎችን፤ የጥበብ ሰዎችን፤ እና በህብረተሰቡ አንቱ የተባሉ ስዎችን በመጋበዝ ሰፊ ተሞክሮዋቸውን እንዲያጋሩ ማድረጋቸውን አዘጋጆቹ ያስረዳሉ፡፡ፕሮግራሙ ተወዳጅ እንደሆነ እንዲቀጥል ለሚያደረጉት ጥረት ማሳያ የሚሆነው ከግጥም በተጨማሪ በአንድ ሰው የሚቀርብ ተውኔት ላለፉት 12 ወራት ሳይቋረጥ መቅረቡን ማየት የሚቻል ሲሆን ይህ በበረከት በላይነህ እየተደረሰ በግሩም ዘነበ የሚቀርበው “እያዩ ፈንገስ” የተሰኘ ዝግጅት በታዳምያን ዘንድም ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡
ባብዛኛው በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ይህ የአንድ ሰው ተውኔት(one man show) የ ጦቢያ ግጥምን በጃዝ ሌላው ተወዳጅ ፕሮግራም መሆኑን አስተያየት ሰጪዎችም ይመሰክራሉ፡፡ በእያዩ ፈንገስ የሚቀርበውን ተውኔት ተቀባይነት በተመለከተም መሀንዲሱ ሀይሉ ተመሳሳይ ማህበራዊ ሂስ የሚቀርብባቸው መድረኮች እጥረት መኖሩን እንደሚያሳይ ይናገራል፡፡ እንደ አገር ወቅታዊ በሆኑ ሃገራዊ አጀንዳዎቻችን እና ተግዳሮቶቻችን ላይ በግልፅ መነጋገርያ አማራጭ መድረኮች እጥረት አለ ብሎም ያምናል፡፡ በማህበራዊ ችግሮች ፤ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ላይ በግልፅ የሚወያዩ መድኮች መብዛት እንዳለባቸውም ያስባል፡፡ ፖለቲካዊ ሂስ ስምን ደብቆ በማህበራዊ ሚድያ እና በግጥም ብቻ መቅረብ አለበት ብሎም አያስብም፡፡ ተመሳሳይ ገንቢ ሂሶች የሚስተናገዱባቸው አማራጭ መድረኮች በጋዜጦችም ሆነ በሌሎች የሚድያ ተቋማት ሊበዙ እንደሚገባም ይናገራል የምህንድስና ባለሞያው ሃይሉ፡፡
ስሙ እንዳይገለፅ የሚናገረው እና በኢትዮጵያ ሚድያ ውስጥ ላለፉት ሰባት አመታት መስራቱን የሚናገረው ጋዜጠኛ ከላይ ከተገለፀው ተመሳሳይነት ያለው ሃሳብ ሰንዝሯል፡፡ ይኧው ጋዜጥኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች በግልፅ ለመነጋገር ሁኔታው አያመችም ብለው የሚያስቡ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያስታውሳል ፡፡ እርሱ እንደሚያስበውም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አማራጭ ሃሳቦች የሚቀርቡበት መድረኮች እጥረት አለ፡፡ ስለችግሮቻችን እንደቀልድ ተደርጎ በግጥም ወይም በዲስኩር መልክ ሲነገር መነጋገርያ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያትም ይመስለዋል፡፡ የልቡን የሚናገረው ደራሲና እብድ ብቻ ነው የሚለውን ተለምዶአዊ አነጋገርም የዚሁ ችግር ማሳያ አድርጎም ያቀርበዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ የጦብያን የመሰለ ግጥም በጃዝ የሚቀርብባቸው መድረኮች መበራከታቸው ስነፅሁፉን ከማሳደግ በተጨማሪ በማህበራዊ ጉድለቶቻችን ላይ ተጨማሪ መነጋገርያ መድረኮች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ የሚልም ግምት አለው፡፡
ግጥምን በጃዝ አዋህዶ የማቅረቡ ጥረት ከአዲስ አበባ አልፎ ለመጀመርያ ጊዜ በአውሮፓዊቷ ሀገር ጀርመን መደረጉን የፕሮግራሙ አዘጋጆች ይናገራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ጋር በትብብር እንደሚሰራ በሚነገርለት በበርሊኑ ዩንቨርስቲ ስር የሚገኘዉ Institut für Raumexperimente በመባል የሚታወቀዉ ተቋም በጋበዛቸው መሰረት ወደጀርመን መሄዳቸውን እና በርካታ ኢትዮጵያዉያን ፤ ጀርመናዉያን እና ሌሎች ከምዕራቡ ዓለም የመጡ ታዳሚዎች በተገኙበት የአማርኛ ግጥሞችን ወደ እንግሊዘኛ እና ጀርመንኛ በመተርጎም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ማስደሰት መቻላቸውን ሰአሊ እና ገጣሚ ምህረት ተናግራለች፡፡