Diriba Kuma, Addis Ababa Mayor
Diriba Kuma, Addis Ababa Mayor
  • ቀድሞው ከነበረው የቆዳ ስፋቷ 2ሺ ሄክታር የት እንደገባ አልታወቀም

ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ ይፀድቃል እየተባለ በርከት ላሉ ወራት ሲንከባለል የቆየው የአዲስ አበባ 10ኛው የከተማ ዐብይ ካርታ (ማስተር ፕላን) የአዲስ አበባን የቆዳ ስፋት ድምር ወደ 52ሺ ሄክታር አጥብቦታል፡፡ ኾኖም ከተማዋ ከ1986 ጀምሮ የነበራት የቆዳ ስፋት 54ሺ ሄክታር እንደኾነ ይታወቃል፡፡ 2ሺ ሄክታር መሬት የት ገባ የሚለውን የሚመልስ ባለሥልጣን እስካሁን ማግኘት አልተቻለም፡፡

አዲስ አበባ ከነበራት የቆዳ ስፋት እንዴት ልትጠብ ቻለች የሚለው ጉዳይ በርካታ የመሬት ልማት ባለሞያዎችን ሲያነጋግር የከረመ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት ክፍለ ከተሞች መሪ ፕላኑን በተናጥል እንዲተቹ የተበተነላቸውን ደብዳቤ ተከትሎ በሰጡት ምላሽና ተያያዥ ማብራሪያ የክፍለ ከተሞቻቸው የቆዳ ስፋት ማነስ ጉዳይ በሦስት ክፍለ ከተሞች ዘንድ ተነስቷል፡፡ ከዚህ በኋላም ቢኾን ጉዳዩ በተለያዩ መድረኮች እየተስተጋባ ቆይቷል፡፡

ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በካፒታል ሆቴልና ስፖ በኋላም በጌትፋም ኢንተርናሽናል ሆቴል ከአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የመሬት ባለሞያዎች ባደረጉት ዉይይት ‹‹የአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት የቀነሰበት ምክንያት ምንድነው? ይብራራልን›› የሚል ጥያቄ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ተነስቶ የነበረ ሲሆን መሪ ፕላኑን በማዘጋጀቱ ረገድ የመሪነት ሚና የነበራቸውና የማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትና በቅርቡ በተዋቀረው በአዲሱ የድሪባ ኩባ ካቢኔ ደግሞ የከተማዋ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ኾነው የተሾሙት አቶ ማቴዎስ አስፋው ጥያቄውን አድባብሰው አልፈውታል፡፡ እንደምታውቁት ልብስም ሲታጠብ መጠኑ እየቀነሰ ነው የሚሄደው፣ አደራ ደግሞ እንደ ኮንዶሚንየሙ መሬቱም ጠፋ እንዳትሉ፣ አንዳንድ የቀሩ ሥራዎች ስላሉ ነው… በማለት … ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በሁለቱም የዉይይት መድረኮች  ጥያቄው ቢነሳም የኾነው ተመሳሳይ ነገር ነበር፡፡ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ የሚሉ ድፍን መልሶች እየተሰጡ ወደ ሌሎች ጥያቄዎች ማለፍ ምናልባት በዉስጥ የፖለቲከኞች ድርድር በኦሮሚያና በፊንፊኔ መካከል መሬትን ሰጥቶ የመቀበል ሂደት እየተካሄደ ይሆን? የሚል መላምት እንዲኖር አስችሏል፡፡

ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡና በዉይይቶቹ የተሳተፉ አንድ የመሬት ባለሞያ የከተማዋ የቆዳ ስፋት መቀነስ እንደዋዛ የሚታለፍ እንዳልሆነ ጠቅሰው ምናልባት ችግሩ የተከሰተው ወደ ፊኒፊኔ ልዩ ዞኖች የገቡ የአዲስ አበባ መሬቶች በመኖራቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አስተያየታቸውን ሲያብራሩም በየካ ክፍለ ከተማ አያት አባዱ አካባቢ ከለገጣፎ የሚያዋስነው ሸለቆ ካልሆነ በስተቀር በተቀሩት ክፍለ ከተሞች በየትኛውም አቅጣጫ ቢኾን የከተማዋ ድንበሮች በትክክል አይታወቁም፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ኾነ ኮልፌ ቀራንዮ፣ አቃቂ ቃሊቲም ኾነ ጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲስ አበባ እያስተዳደራቸው በኦሮሚያ መሬት ላይ ያሉ፣ እንዲሁም ኦሮሚያ እያስተዳደራቸው አዲስ አበባ መሬት ላይ ያሉ ሰፈሮችና ቀበሌዎች በብዛት እንዳሉ አውስተዋል፡፡ እንደምሳሌ ያነሱትም ከዚህ ቀደም 25 ሄክታር የሚኾን ቦታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ለአዲስ አበባ የ20/80 ኮንዶሚንየም ግንባታ ከተከለለ በኋላ መሬቱ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነው በሚል መቆሙን እንደሚያውቁ እኚሁ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ቢሮ የሚሰሩ ሲኒየር ኦፊሰር ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አበባን ከፊንፊኔ ልዩ ዞኖች የሚለዩ ችካሎችም ሆኑ የተፈጥሮ ምልክቶች እምብዛምም አይገኙም፡፡ ሁሉቱ መስተዳደሮች ቁጭ ብለው ዉሳኔ ካልሰጡ ወደፊት ሌላ ዙር የይገባኛል ጥያቄ መፈጠሩ የማይቀር ነው ባይ ናቸው ባለሞያው፡፡

ያም ኾነ አዲስ አበባ በ1953 ከነበራት የ22ሺ ሄክታር ስፋት ተነስታ በ1986 ከ54ሺ ሄክታር ጥቂት ከፍ ያለ የቆዳ ስፋት ኖሯት አሁን እንዴት ስፋቷ ሊቀንስ ይችላል? በአንዳንድ አሰራሮች ምክንያት ቀነሰ ቢባል እንኳ እንዴት 2ሺ ሄክታር ያህል የቆዳ ስፋት በአንድ ጊዜ ሊቀንስ ይችላል የሚለው ለብዙዎች መልስ ያላገኘ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በድንበር አካባቢ ወደ ኦሮሚያና ወደ አዲስ አበባ ገባ ወጣ የሚሉ ቀበሌዎች እንዴትም በቁጥር በርካታ ቢኾኑ 2ሺ ሄክታር ያህል ስፋት ሊኖራቸው አይችልም የሚሉ ሌላ አስተያት ሰጪ ምናልባት ዉስጥ ለውስጥ የተወሰኑ መሬቶች በኦሮሚያ ሥር እንዲሆኑ ድርድር ተካሄዶ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ጥርጣሬ ያንጸባርቃሉ፡፡ አዲስ አበባ ባለቤት አልባ ከተማ ናት፣ ከኦሮሚያ መሬት ቆርሰህ ለአዲስ አበባ ከምትሰጥ ከአዲስ አበባ ቆርሰክ ለኦሮሚያ መስጠት ከወቅቱ  የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተያይዞ ትክክለኛ ፖለቲካዊ ዉሳኔ ነው ፤ ምናልባት ያ ተደርጎ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የምገምተው ይላሉ እኚሁ ግለሰብ፡፡

2ሺ ሄክታር የልደታ ክፍለ ከተማን ሁለት እጥፍና ከዚያም በላይ የሚያህል ቦታ ማለት ነው፡፡ የልደታ ክፍለ ከተማ የቆዳ ስፋት 800 ሄክታር ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከቡራዩ ልዩ ዞን ጋር በቦታ ይገባኛል ጥያቄ መነታረካቸው ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሰበታ ጋር ተመሳሳይ የድንበር አለመግባባቶች ተፈጥረው መፍትሄ ሳያገኙ ታልፈዋል፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ የሚያስታደድራቸው በፉሪ ከተማ የሚገኙ ቦታዎች ከኦሮሚያ ጋር መጠቃለላቸው ከሁለት ዓመት በፊት ጭቅጭቅ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚያው በፉሪ አካባቢ ፋይላችሁ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ይተላለፍላችኋል፣ ጠብቁ ተብለው የነበሩ አባወራዎች እንደነበሩና፣ መሬታቸውም ወደ አዲስ አበባ ሊጠቃለል ስለሆነ በሚል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቤት በዉድ ይሸጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የቀድሞው ርዕሰ ብሔር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድ ወቅት ለሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደተናገሩት በደርግ ጊዜ አዲስ አበባን ግዙፍ ከተማ ለማድረግ የማስፋፋት ሥራዎች ሂደት ላይ እንደነበሩና የከተማዋን ድንበርም ወልቂጤ፣ አምቦ፣ ናዝሬት ድረስ እንዲሆን ታስቦ እንቅስቃሴ መጀመሩን አውስተዋል፡፡ በሽግግሩ ጊዜ ግን አዲስ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ የኦሮሚና የአዲስ አበባ ድንበር በግልጽ እንዲካለል ተወስኖ እንደነበረና ያ ሥራ እስከዛሬ መካሄድ አለመካሄዱ ላይ ግን መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

10ኛው ማስተር ፕላን በሳምንታት ዉስጥ እንደሚጸድቅ ሲጠበቅ 9ኛው ማስተር ፕላን የትግበራ ጊዜው ካበቃ ሦስት ዓመታት እንደዋዛ አልፈዋል፡፡ አሁን ከተማዋ እየተመራች ያለችው ለካቢኔ ቀርቦ ባልፀደቀውና ገና ዉይይት ላይ ባለው 10ኛው ማስተር ፕላን ነው፡፡ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና በማዘጋጃ ቤት የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ቢሮዎች የሕንጻዎች የግንባታ ከፍታ እየተወሰነ ያለውም ያልፀደቀው ማስተር ፕላን በሚያዘው መሠረት ብቻ ነው፡፡