One of the recently built complexes in Addis, Churchill Road -Wazema
One of the recently built complexes in Addis, Churchill Road -Wazema

ከንቲባ ድሪባ በጥቂት ቀናት 1ሺህ 300 ቤቶችን ያፈረሰውን ቂርቆስ ክ/ከተማን አወደሱ

ዋዜማ ራዲዮ-የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ተጨማሪ ወራት መራዘሙን ተከትሎ የአዲስ አበባ ካቢኔ አስቀድሞ የያዘውን ቤቶችን በስፋት የማፍረስ ምስጢራዊ እቅድ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡  እቅዱ ሁለት መልክ ያለው ሲሆን የመጀመርያው ነባርና ጥንታዊ የከተማዋን ማዕከላዊ ሰፈሮች እያፈረሱ ለአገር ዉስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎች በፍጥነት ሸንሽኖ መስጠት ሲሆን ሁለተኛው እቅድ ደግሞ ከማስፋፊያ ሠፈሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ይህ ዕቅድ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገበት የሚገኝ እንደሆነ ሲታወቅ ከ1988 እስከ 1997 በአየር ካርታ የተመላከቱ ይዞታዎችን ወደ ሕጋዊነት አስገብቶ ጊዝያዊ የይዞታ ቢሮዎች በተቻለ ፍጥነት መዝጋት፣ እንዲሁም 1997 ወዲህ በከፊል፣ በተለይም ከ2003 ዓ.ም በኋላ ያለ መስተዳደሩ እውቅና በወረራ የተገነቡ 30ሺህ የሚጠጉ ሕገወጥ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በዘመቻ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የማፍረስ ተግባርን ያካተተ ነው፡፡ ይህ ተግባር ለሁከት ምክንያት በማይሆን ሁኔታ በጥንቃቄ እንዲፈጸም ይፈለጋል፡፡

ለዚህም ሲባል ከወራት በፊት ለቤትና ሕዝብ ቆጠራ ጥቅል መረጃ ለመሰብሰብ ነው በሚል ሽፋን ሕገወጥ ሰፋሪዎች የሚበዙባቸው ሰፈሮችን ቤት ለቤት በመሄድ ቤተሰቡ ዉስጥ የሚገኙ የወጣቶችን ብዛት፣ ስምና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች በወረዳና በክፍለ ከተማ የድርጅት አባላት ቅንጅት እንዲሰበሰቡ ሲደረጉ ቆይቷል፡፡

በ1988 እና በ1997 በአየር ካርታ የተመላከቱ ሕገወጥ ቤቶችን ወደ ሕጋዊነት (Regularization) ለመውሰድ በተሞከረው ሂደት ቀደም ብለው በወረራ ተይዘው የተገነቡ 20ሺ ይዞታዎች ካርታ ቢዘጋጅላቸውም ግማሽ የሚኾኑት ነዋሪዎች ብቻ ካርታ ለመውሰድ ችለዋል፡፡ በርካቶች ግን ወደ ሕጋዊነት ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን ገንዘብ ማግኘት ባለመቻላቸው እድሉን ሊጠቀሙበት እንዳልቻሉ መስተዳደሩ ባደረጋቸው የሕዝብ ዉይይቶች ተመልክቷል፡፡ ይህ ወደ ሕጋዊነት የማሸጋገሩ ተግባር 150 ካሬ ቦታን በሊዝ መነሻ ዋጋ፣ ቀሪ ቦታን ደግሞ በአካባቢው አማካይ የሊዝ ዋጋ መክፈል የሚጠይቅ ሲሆን የወለድ ተመኑም ከፍ ያለ ነው፡፡  ይህም በመሆኑ በርካታዎች ያገኙትን እድል ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ለመስጠት እየተገደዱ ነው፡፡

መሐሉን የከተማዋን ክፍል የማፍረሱ ተግባር በችግሮች የተተበተበና የሕዝብ ቅሬታን እያመጣ በመኾኑ ለጊዜው እንዲቆም ተወስኖ የነበረ ሲሆን አሁን ሁኔታዎች በመረጋጋታቸው ከሁለት ሳምንት በፊት አቶ ለዓለም የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መሠረታዊ ችግሮችን የሚፈቱ የዉሳኔ ሐሳቦችን ለካቢኔው ይዞ በማቅረብ በመልሶ ማልማት የማስነሳት ተግባር በፍጥነት እንዲጀመር ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ ችግሮች ከካሳ፣ ከተነጻጻሪ ካርታና ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያያዙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የመልሶ ማልማት ተግባር አሁን ባለው የፖለቲካ አውድ ቤንዚል የማርከፍከፍ ያህል ነው በሚል ሂደቱ እንዲዘገይ ያሳሰቡ የካቢኔ አባላት እንደነበሩ ተሰምቷል፡፡ ኾኖም ብዙዎች ሂደቱ አሁን ካልተካሄደ መቼም ሊካሄድ የሚችል አይደለም፤ ድርጅታችን የሚወደስበትን የከተማዋን ፈጣን እድገትም በአጭር መቅጨት ይሆናል በሚል መከራከርያ አቅርበዋል፡፡

የከንቲባ ድሪባ ኩማ አስተዳደር በሆስፒታል፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሞል፣ በሪልስቴትና በሆቴል ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት ለመሳተፍ በሚፈልጉ የሩቅ መሥራቅና የቱርክ ባለሐብቶች ጥያቄ ተሰንጎ ቆይቷል፡፡ ኾኖም እነዚህን ከፍተኛ ባለሐብቶች ለማስተናገድ የሊዝ አዋጁን ማሻሻልና በመሐል ከተማ የመሬት አቅርቦትን በሚፈለገው ደረጃ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡

የሊዝ አዋጁ መሬት የሚሰጥበት አግባብ በጨረታ ብቻ እንዲሆንና ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ባለሐብቶች ግን በድርድር እንዲያገኙ የሚጠቁም አንቀጽ ቢኖረውም ካለው ከፍተኛ የመሬት ጥያቄ የተነሳ እምብዛምም የሚያሠራ ባለመሆኑ አዲስ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት  እንዲጸድቅ ወረፋ እንደያዘ በማዘጋጃ ቤት የመሬት ዝግጅት ዉስጥ የሚሠሩ አንድ የመሬት ባለሞያ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ አዋጁ ከሰኔ በፊት እስኪጸድቅ በመሐል ከተማ የሚገኙ ቦታዎችን በስፋትና በአጭር ጊዜ ዉስጥ አፍርሶ ለልማት ዝግጁ ማድረግ አቅጣጫ የተሰጠበት ጉዳይ እንደሆነም እኚሁ ባለሞያ አብራርተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ካለፉት 15 ቀናት ወዲህ ሜክሲኮ ገነት ሆቴልን ይዞ ቄራ መንገድ እስከ ቡልጋሪያ ያሉ ሰፈሮችን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ዉጤታማ ሥራ እንደተሠራ ተወስቷል፡፡ ይህ በወረዳ 11 በቀድሞው አጠራር ቀበሌ 9 ቡልጋሪያ ሰፈር የሚገኘው ቦታ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ፈራርሶ ይታያል፡፡ አጋጣሚው ከኳታሩ ንጉሥ ታሚም ቢል ሃማድ አልታኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር መገጣጠሙ ቦታው ለኳታር ባለሐብቶች ተፈልጎ ነው የሚል ሀሜት በነዋሪዎች ዘንድ በስፋት እንዲነገር አስችሏል፡፡ ኾኖም የዋዜማ ሪፖርተር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ኦፊሰሮችን አናግራ ባገኘችው መረጃ ቦታው ለየትኛው አልሚ ይሰጥ የሚለው ጉዳይ ገና ዉሳኔ ያላገኘ ነው፡፡

በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ የማፍረስ ተግባር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት በከንቲባ ድሪባ ኩማ ተወድሶበታል፡፡ “አንድም ጫጫታ ሳንሰማ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እቅድ ማስፈጸም መቻሉ ምን ያህል አቅደው ከሕዝብ ጋር ተወያይተው መሥራታቸውን ያሳያል፤ ይህ ለሌሎቻችሁም አርአያነት ያለው ተግባር ነው” ሲሉ አቶ ድሪባ በማዘጋጃ ቤት የካቢኔ አዳራሽ ዉስጥ ለተሰበሰቡ ከ60 ለማይበልጡ መካከለኛና ከፍተኛ የመሬት ባለሞያዎች የተናገሩት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

የከንቲባውን ዉዳሴ ተክትሎ በእንጥልጥል ቆመው የነበሩ ሰፈሮችን በፍጥነት ለማፍረስ የአራዳ፣ የየካ፣ የአዲስ ከተማና የቦሌ ከፍለ ከተሞች በከፍተኛ የቅድመ ፈረሳ ሥራ ተጠምደዋል፡፡ የካ ክፍለ ከተማ አቧሬ ሚስፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢን፣ አራዳ ክፍለ ከተማ 2ሺ የሚጠጉ ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈርና እሪ በከንቱ የሚገኙ ቤቶችን፣  ቂርቆስና ቦሌ ክፍለ ከተማ በጋራ ካዛንቺስና ዙርያውን፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰባተኛን፣ አብነትና አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ፣ የቀድሞው 32 ቀበሌና አካባቢውን፣ ቂርቆስና አራዳ ክፍለ ከተማ ሊሴ ገብረማርያም ጀርባ የሚገኙ ሰፋፊ ይዞታዎችን እንዲሁም ከአምባሳደር ቴአትር ጀርባ የተኮለኮሉ በተለምዶ ኦርማ ጋራዥ የሚባሉትን ሰፈሮች የማፍረስ ዉጥን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

ኦርማ ጋራዥና አካባቢው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አዲስ ሕንጻ አስገንብቶ እየሠራበት የሚገኝ ሲሆን በዙርያው የሚገኙ አጎራባቹ ሰፈሮች እንዲፈርሱለትም ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም የአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየምና የልቀት ማዕከልን ለመገንባት በመፈለጉ ነው፡፡ መስተዳደሩ ለዚሁ ተግባር የሚውል 30ሺህ ካሬ ቦታ ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ እንዳስረከበ ይታወቃል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችም ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ ቤቶቻቸውን ማፍረስ ጀምረዋል፡፡ በአካባቢው በአሁን ሰዓት የሚታየውም በመፍረስ ላይ ያሉ ቤቶች ፍርስራሽ ነው፡፡

እስከ አሁን በተኬደበት አሰራር ቤታቸው የሚፈርስባቸው ነዋሪዎች የቀበሌ ቤት አልያም ኮንዶሚንየም እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ ኮንዶሚንየም እስኪሰጣቸው ደግሞ ለአንድ ዓመት የትራንስፖርት 11ሺህ ብር፣ ለቤት ኪራይ ደግሞ 31ሺህ ብር ይለገሳቸዋል፡፡

ኾኖም የአካባቢው ማስተር ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመገንባት አቅም አለን የሚሉ ተነሺዎች ካሉ እድሉ ከሞላ ጎደል  ይመቻችላቸዋል፡፡ ኾኖም ይህ አጋጣሚ የሚፈጠርበት እድል እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በመሀል ከተማ እንደ ቡልጋሪያ ባሉ ሰፈሮች አዲሱ ማስተር ፕላን ዞን አንድ ዉስጥ የሚያካትታቸው ሲሆን በነዚህ ሰፈሮች አንድ ተነሺ የማልማት አቅም አለኝ ካለ ከ9 እስከ 19 ወለል ያለው ፎቅ እንዲገነባ ያስገድደዋል፡፡ ይህ ለብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰማይ ያህል ሩቅ የሆነ ሐሳብ ነው፡፡

የመስተዳደሩ መመሪያ ቁጥር 19/2006 የልማት ተነሺዎች መጀመርያ ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸውና ከዚያ በኋላ ደግሞ ካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ያዛል፡፡ ምትክ የሚሰጡ ቦታዎችም ተነሺዎች ይኖሩባቸው ከነበሩ ሰፈሮች ብዙም የማይርቁ፣ ሁሉም ዓይነት መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆን እንዳለባቸው ቢደነግግም በአሠራር ደረጃ ግን ይህ ደንብ የተከበረበት አጋጣሚ የለም፡፡ ተነሺዎች የከተማዋ ጠረፍ ተወስደው እንዲሰፍሩ ይደረጋሉ፡፡

እንደ ምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት በቡልጋሪያ ቤት የፈረሰባቸው ተነሺዎች ምትክ ያገኙት አያት ፀበል ጣፎ መውጫ የኦሮሚያ ድንበር ላይ ሲሆን አሜሪካን ግቢ ተነሺዎች በበኩላቸው ካራቆሬ አጃምባ በመባል የሚታወቅ የኦሮሚያ ድንበር ላይ የተገነባ ኮንዶሚንየም ሳይት ነው፡፡ ይህ ዜጎችን ለ30 እና 40 ዓመታት ከኖሩበት ቀዬ በዘፈቀደ አፈናቅሎ የከተማው ዳርቻ ወስዶ መጣል ከፍተኛ የኑሮና ማኅበራዊ ሕይወት መስቅልቅልን እንደፈጠር ይታመናል፡፡

ለግል ቤት ባለይዞታ ተነሺዎች የካሳ ተመን ሌላው የነዋሪዎች ቅሬታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማክሰኞ ሚያዚያ 10 ለታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃል የካሳ ተመኑ ማሻሻያ እንደተደረገበትና ከ144ሺ ዝቅተኛ የካሳ ተመን ወደ 255ሺ ብር ከፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡  ይህ ተመን ከአምናው ጋር ሲወዳደርም የ9 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ የወቅቱ የቤት ማሰሪያ ተመን ከዚህ በ20ና በ30 እጥፍ እንደሚሆን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የከንቲባ ድሪባ ኩማ መስተዳደር በማስፋፊያ ቦታዎች ለሚደረግ መጠነ ሰፊ የማፍረስ ተግባር ሰፊ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከቆሼ የመደርመስ አደጋ በኋላ በሕዝብ ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል በሚል አዲስ ስልት የተቀየሰ ሲሆን ከመጠለያቸው የሚፈናቀሉ የድሀ ድሀ የሆኑ ነዋሪዎችን ለማስጠለል ዝግጅት ተጀምሯል፡፡

ይህ ግዙፍ እንደሆነ የተነገረለት በመጋዘን ቅርጽ የተሠራ የጋራ መጠለያ በ82 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡ ይህ የመጠለያ መጋዘን ቤት ከፈረሰባቸው በኋላ ጎዳና ሊወድቁ ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱ ነፍሰ ጡሮች፣ አካል ጉዳተኞችና ምንም ዓይነት ቤሳቤስቲ ለሌላቸው የከተማዋ ተነሺ ነዋሪዎች እንዲሆን ታስቦ ለአረንጓዴ ቦታ በተያዘ መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን ወደፊት ዘላቂ መፍትሄ ሲገኝ ነዋሪዎቹ መጋዘኑን እንዲለቁ ይደረጋል ተብሏል፡፡ የዚህ የድሀ ድሀዎች መጠለያ መጋዘን ግንባታ በአሁኑ ሰዓት እየተፋጠነ ሲሆን ግንባታው እየተካሄደ ያለውም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ተክለኃይማኖት በሚባል ጠረፋማና ተራራማ ሥፍራ ነው፡፡

መንግሥት የመልሶ ማልማትና የሕገወጥ ቤቶች ግንባታ የማፍረስ ተግባር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመጠናቀቁ በፊት በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት እንዳለው ዋዜማ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል፡፡