addis-ababa-street

  • ከሰሞኑ አዲስ የፉርኖ ዱቄት እጥረት ተከስቷል፡፡
  • ባለሱቆች ስኳር የሚሸጡለትን ዜጋ ሙሉ አድራሻ እንዲይዙ ተነግሯቸዋል
  • የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት የሌላቸው ዜጎች ስኳር መግዛት አይችሉም

ዋዜማ ራዲዮ- ከአውድ ዓመት መቃረብ ጋር ተያይዞ ለስኳርና ዘይት ግዢ በየወረዳው የሚገኙ የሸማች ማኅበራት ሱቆች ታይቶ የማይታወቅ ረዣዥም ሰልፎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ በአንዳንዶቹ የኅብረት ሱቆች ወረፋ ከሌሊት ጀምሮ መያዝ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በጎላ ሚካኤል ሸማቾች ማኅበር ሰልፍ ከሌሊቱ 11 ሰዓት የሚጀምር ሲኾን የሸማቾች ማኅበር ሱቅ የሚከፈተው ደግሞ ከጠዋቱ 2፡30 በኋላ ነው፡፡

ስኳር ከሸማቾች ማኅበር ዉጭ ባለ ጥቁር ገበያ እስከ 26 ብር በኪሎ ይሸጣል፡፡ ኾኖም ባለሱቆች በዚህ ዋጋ መሸጣቸው በሕግ እንደሚያስጠይቃቸው ስለሚረዱ ለማያውቁት ደንበኛ በየትኛውም ዉድ ዋጋ ስኳር ለመሸጥ አይፈቅዱም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ባለሱቆች ስኳር የሸጡለትን ሰው ሙሉ ስም፣ የቤት ቁጥርና ሙሉ የስልክ አድራሻውን መዝግበው እንዲይዙ ከወረዳ ኃላፊዎችና ደንብ አስከባሪዎች ታዘናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በየወረዳው ከ5 እስከ 10 የሸማች ማኅበራት ሱቆች ቢኖሩም ከስኳር ፈላጊው ዜጋ ቁጥር ጋር ሊመጣጠኑ አልቻሉም፡፡

ዜጎች ስኳር፣ ዘይትና የፉርኖ ዱቄት ከነዚህ የሸማች ማኅበራት ሲገዙ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ሊኖራቸው የግድ ነው፡፡ ፓስፖርት አንቀበልም፣ የቀበሌ መታወቂያ ካልሆነ የሚሉ የሸማች ማኅበራት እንዳሉም ለማረዳት ችለናል፡፡ ነዋሪዎች እነዚህን ሸቀጦች መግዛት የሚችሉት የመታወቂያ አድራሻቸው ከሚገኝበት ሱቅ ብቻ መሆኑን ሌላ ፈተና እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከድሬዳዋ እንደመጣ ለዋዜማ ሪፖርተር የገለጸውና በሞያው መምህር የኾነው አቶ የሺዋስ በሸጎሌ የሸማቾች ማኅበር ከረዥምና እጅግ አታካች ሰልፍ በኋላ ስኳር ለመግዛት ቢሞክርም የቀበሌው ቋሚ ነዋሪ ካልሆንክ አይቻልም በሚል እንደተከለከለ ይናገራል፡፡ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ከድሬዳዋ መሸኛ ይዘህ ካልመጣህ ስኳር አንሸጥልህም ብለውኛል ይላል፡፡ “ሻይ አፍልቼ ለመጠጣት ኢትዮጵያዊ መኾኔ አይበቃም ወይ? ብላቸውም ሊሰሙኝ ፍቃደኛ አልሆኑም ሲል በመገረም የደረሰበትን ያብራራል፡፡

በዙዎቹ የሸማቾች ማኅበራት በሳምንት ማክሰኞ ብቻ ስኳርና ዘይት እንደሚራገፍና ይህ በማይሆንበት ጊዜ ግን የአካባቢው ነዋሪ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቸገር ይነገራል፡፡ ዘወትር ማክሰኞ ሸቀጥ ገባ ከተባለ ነዋሪዎች በስልክና በተለያዩ መንገዶች ተደዋውለው ሰልፍ ለመያዝ እንደሚሯሯጡና ወረፋ ላይ መረባበሽ ስለሚከሰት ይህን እንዲቆጣጠሩ ፖሊሶች እንደሚመደብ ታውቋል፡፡

ቀኑን ሙሉ ተሰልፎ ተራ የደረሰው አንድ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ያለው ዜጋ በአንድ ጊዜ መግዛት የሚችለው 2 ኪሎ ብቻ መኾኑን የዋዜማ ሪፖርተር በተዘዋወረችባቸው ቀበሌዎች ጠይቃ ለመረዳት ችላለች፡፡ አንድ ኪሎ የስኳር ዋጋም ከትናንት በስቲያ 18 ብር ከ20 ሳንቲም ገብቷል፡፡ የፉርኖ ዱቄት አንደኛ ደረጃና 2ኛ ደረጃ ያለው ሲኾን ደረጃ አንድ 8 ብር ከ50 ይሸጣል፡፡

“የዘይት፣ የፉርኖ ዱቄት፣ ስኳር የሚገዙ ነዋሪዎች ለዚሁ በተዘጋጀ መዝገብ ሙሉ አድራሻቸው ይመዘገባል፡፡ ይህም የሚኾነው ሕገወጥ ነጋዴዎች ከሸማች ማኅበራት በቅናሽ እየገዙ የዋጋ ንረት እንዳይፈጥሩ በሚል ነው” ብላለች ለዋዜማ ሐሳቧን ያጋራችና ፒያሳ ካቴድራል ቶሞካ ፊትለፊት በሚገኝ የሸማቾች ማኅበር ሠራተኛ የኾነች አንዲት ወጣት፡፡ አንድ ቤተሰብ የተለያዩ ልጆቹን እየላከ ብዙ ኪሎ ስኳር ሊወስድ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌሎች ቤተሰቦች ጦማቸውን እንዲዉሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ለነዋሪው ለራሱ ብለን ነው ቁጥጥር የምናደርገው ትላለች ይህቺው የማኅበሩ ሠራተኛ፡፡

ዘይት ባለ 3፣ ባለ 5 እና ባለ 20 ሊትር በቢጫ ጄሪካን እየታሸገ የሚሸጥ ሲኾን ባለ 3 ሊትሩ 71 ብር ከ25 ሳንቲም፣ ባለ 5 ሊትሩ 130 ብር እንዲሁም ባለ 20 ሊትሩ 320 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከሸማቾች ማኅበራት ዉጭ የነዚህ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ መርካቶ ባለ 3 ሊትሩ እስከ 200 ብር እየተቸበቸበ እንደሚገኝ ለመረዳት ችለናል፡፡

የሸማቾች ማኅበራት የዋጋ ንረትን ለማስቀረትና ለነዋሪዎች መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ታልመው የተከፈቱ ቢኾንም ነዋሪዎች በበቂ ሆኔታ ሳያገኙ “አልቋል” በማለት በድብቅ በሌሊት እያወጡ ለነጋዴዎች ይሸጣሉ፣ ኪራይ ሰብሳቢ ኾነዋል በሚል ስሞታ ሲቀርብባቸው ቆይቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ከሰሞኑ ከነዋሪዎች ጋር “ጥልቅ ተሀድሶ” እየተካሄደባቸው በሚገኙ የክፍለ ከተማ የነዋሪዎችና የሹማምንት ዉይይቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ  ነው፡፡ መንግሥት በበኩሉ እንዲህ የሚያደርጉ ኃላፊዎች ካሉ ኅብረተሰቡ ጠቁሞ እንዲያሲዛቸውና ወዲያዉኑ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ለሕግ እንደሚቀርቡ ቃል ገብቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ መንግሥት 140ሺ ሜትሪክ ቶን ስኳር 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከሕንድ ግዢ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ፊንጫ፣ መተሀራና ወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች ከኢሊኖና ኢሊኖ ካስተከተለው ጎርፍ ጋር በተያያዘ በቂ ምርት እንዳላመረቱ ይነገራል፡፡ ከነዚህ ዉጭ 7 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ናቸው ቢባልም የግንባታ ሂደታቸውና ፋብሪካዎቹን ለማቆም የወጣው ወጪ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ዉዝግብ ሲያስነሳ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መዘግየትና ብክነት ተጠያቂ ነው የሚባለው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በዝምታ መታለፉም በርካታ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል፡፡

ይህን ፖለቲካዊ ዉዝግብ ተከትሎም መንግሥት እገነባቸዋለሁ ብሎ ካቀዳቸው 7 የስኳር ፋብሪካዎች ዉስጥ በፋይናንስ እጥረት የተነሳ ሁለቱን መሠረዙን ከሦስት ወራት በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡

በኢህአዴግ መንግሥት ከፍተኛ ምዝበራና የሕዝብ ሐብት ብክነት ተፈጽሞባቸዋል ተብለው ከሚገመቱ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ዉስጥ የሰባቱ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ቅድሚያ እንደሚይዙ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡