Adanech-Abebe
Mayor Adanech Abeibe- FILE

ዋዜማ- ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪ በሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ተደራጅተው የመኖርያ ቤት እንዲሰሩ የሚያስችል ዕቅድ ወጥቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ለመረዳት ችላለች።

 የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ ውሳኔ መስጠቱም ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ  ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ የመንግስት ተቋማት ያሉ ሰራተኞችን የቤት ፍላጎት የሚያሳይ መረጃ እንዲላክለት ለክፍለ ከተሞች ፣ ለትምህርት ዘርፍ ተቋማት ፣ ለጤና እና ሁሉም የከተማው ቢሮዎች ደብዳቤ ልኮ ከመስሪያ ቤቶቹም የፍላጎት ማሳያ ፎሮሞችን እየሰበሰበ መሆኑንም ተረድተናል።

የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በማህበር በመደራጀት የቤት ተጠቃሚ ለመሆን ለሚፈልጉ በአስተዳደሩ ስር ላሉ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች አንድ ቅድመ ሁኔታን አስቀምጧል። በማህበር ተደራጅቶ የቤት ባለቤት ለመሆን የፈለገ የከተማ አስተዳደሩ ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በእርሱም ሆነ በትዳር አጋሩ ስም የተመዘገበ የመኖርያ ቤት አለመኖሩ መረጋገጥ አለበት። 

ይህም ብቻ ሳይሆን አሁን በማህበር ተደራጅቶ የመኖርያ ቤት ባለቤት ለመሆን የፈለገ ሰራተኛ የ40/60 እና 20/80 ተመዝጋቢ ሆኖ ቤት ቤት ያልደረሰው ከሆነም ለሁለቱ የቤት መርሀ ግብሮች ተመዝግቦ የሚቆጥብበትን የባንክ ሂሳብ ማሳወቅ እንደሚገባው በፍላጎት ማሳወቂያ ቅጽ ላይ ተቀምጧል። ይህም ተደራራቢ የቤት እድል ተጠቃሚነትን ለመቆጣጠር ታስቦ እንደሆነ ተገንዝበናል።

በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ በስሩ ለሚገኙት የመንግስት ሰራተኞች ቤት መስሪያ መሬት እና ብድር ወደ ማመቻቸት የሚያመራ ሲሆን ዝርዝር አፈፃፀሙ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። 

በከተማ አስተዳደሩ ከ1997 አ.ም ጀምሮ ቀጥሎም በ2005 አ.ም በድጋሚ በተደረገ የጋራ መኖርያ ቤት ምዝገባን መነሻ በማድረግ ለ14 ዙር የ20/80 እና ለሶስት ዙር የ40/60 ዕጣ ቢወጣም  ከቤት ፈላጊው ቁጥር አንፃር አሁንም በርካታ ሰው በተስፋ እየተጠባበቀ ይገኛል

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2005 አ.ም በድጋሚ በተደረገ የጋራ መኖርያ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከ900 ሺህ በላይ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ20/80 እና 40/60 መርሀ ግብር መኖርያ ቤትን ማዳረስ እንደሚከብደውና ሌሎች አማራጮችን ለማየት እንደሚገደድ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።  [ዋዜማ]