Ethiopia, Sudan and Egypt leaders April 2015
Ethiopia, Sudan and Egypt leaders April 2015

(ዋዜማ ራዲዮ) የኢትዮዽያ መንግስት የህዳሴ ግድብን ግንባታ መጀመር ተከትሎ ከግብፅ ጋር አለማቀፍ ትኩረትን ወደ ሳበና የተካረረ ውዝግብ መግባታቸው ይታወሳል። ውዝግቡን ለመፍታት የተለያዩ ድርድሮች እየተካሄዱ ነው። ስምምነቶችም ተፈርመዋል።

ከሰሞኑ በካርቱም አንድ ተጨማሪ ስምምነት ተፈርሟል። ስምምነቱ የኢትዮዽያን ጥቅም ይጎዳል የሚሉ ወገኖች ስጋታቸውን እየገለፁ ነው። በስምምነቱ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ይዛው ከነበረው አቋም አፈግፍጋለች እየተባለም ነው። ለመሆኑ የሰሞኑ ስምምነት ይዘት ምንድ ነው? በእርግጥስ ኢትዮጵያ የአቋም ለውጥ አድርጋለች?

አርጋው አሽኔ ዝርዝር አዘጋጅቷል  አድምጡት

ከሰሞኑ በሱዳን ካርቱም የተፈረመው ስምምነት የኢትዮዽያ መንግስት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉት አማካሪዎችን ግኝት መሰረት ያደረገ ውሳኔን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን የገለፀበት ነው። የአማካሪዎቹ ግኝት የግድቡ መጠን ይቀነስ አልያም ይቋረጥ የሚል ሊሆን ይችላል። ይህን ስምምነት በመፈረም መንግስት ራሱን ለትልቅ ፈተና አጋፍጧል። የሀገሪቱን ጥቅምም አሳልፎ ለመስጠት በሩን ከፍቷል።

በሌላ በኩል የግድቡ ስራ እንደቀጠለ ነው። ምንም አይነት አዲስ ውሳኔ ቢመጣ የግድቡን ስራ እንደሚገፋበት እየገለፀ የሚገኘው መንግስት ከወራት በፊት የፈረመው ስምምነት Declaration of Principles የህግ አስገዳጅነት ሊኖረው እንደሚችል የህግ ባለሙያዎች ያሰምሩበታል። የሰሞኑ ስምምነት ቀደም ያለውን Declaration of Principles ለማስፈፀም ያለመ በመሆኑ ሁኔታው ኢትዮዽያ የአቋም መለሳለስ ወይም ማፈግፈግ ማድረጓን ጠቋሚ ነው። በሀገር ጥቅሞች ዙሪያ መልካም ስም የሌለውና ሚስጥራዊነት የሚያበዛው ኢህአዴግ በጉዳዩ ዙሪያ ከዕለት ጉርሱ መዋጮ እየከፈለ ላለው ህዝብ መረጃ መስጠትም አልወደደም። ይልቁንም ስለጉዳዩ ኣኢትዮዽያውያን እየሰሙ ያሉት ከግብፅ መገናኛ ብዙሀን ነው።