Late PM Meles Zenawi inaugurate AYKA Addis in 2010
  • ድርጅቱ ከልማት ባንክ የወሰደውን 2.3 ቢሊየን ብር ዕዳ መክፈል አልቻለም
  • በኢትዮጵያ ከስሪያለሁ ቢልም በቡርኪና ፋሶ ግዙፍ ፋብሪካ መገንባት ጀምሯል

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ሲገባ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ በስራ እድል : በውጭ ምንዛሬ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ብዙ ለውጥ እንደሚያመጣ ተነግሮለት የነበረው የቱርኩ አይካ አዲስ ቴክስታይል ኤንድ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረውን ከ2.3 ቢሊየን ብር በላይ መክፈል ባለመቻሉ የስራ አመራሩን ወይንም የማኔጅመንቱን ቦታ አበዳሪው ልማት ባንክ ወስዶታል። ፋብሪካው በራሱ እና በውጫዊ ችግሮች ሳቢያ ያለው አፈጻጸም እጅግ የወረደ ሆኗል።ኩባንያውን ሲመሩት የነበሩት የሱፍ አይደኒዝ በልማት ባንኩ ወኪሎች መተካታቸውን ምንጮቻችን ነግረውናል።

በአውሮፓውያኑ 2010 ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ብዙ የተባለለት አይካ አዲስ በ240 ሚሊየን ዶላር በኦሮሚያ ክልል በአለም ገና ከተማ ፋብሪካ አቋቁሟል።ሆኖም ለጥቂት ጊዜያት የተወሰነ ትርፍና የውጭ ምንዛሬ ካስገኘ በሁዋላ ለተከታታይ አመታት ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሞኛል እያለ ለመንግስት ሪፖርት ሲያቀርብ ነበር። በአራት አመቱ ያስመዘገበው ኪሳራም ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተነግሯል።በዚህ ምክንያት አይካ አዲስ ለኢትዮጵያ አይደለም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረውን 2.3 ቢሊየን ብር መመለስ አቅቶት የተበላሸ ብድር ውስጥ የመዘገበ ትልቅ ተበዳሪ ሆኗል። ዋዜም ራዲዮ በቅርቡ እንደዘገበችው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ያበደረውን 51.6 በመቶ ሆኗል። ይህም በገንዘብ ሲተመን ባንኩ ካበደረው ከ39 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ 20 ቢሊየን ብሩ ተበላሽቷል ።

የቱርኩ አይካ አዲስ መመለስ ያቃተው ብድር ታድያ ብቻውን ከ10 በመቶ በላይ የባንኩን የተበላሸ ብድር ምጣኔን ይይዛል።ለልማት ባንኩ የከፍተኛ ችግር ምንጭም ሆኗል።አይካ አዲስ ቀድሞ ችግር ውስጥ እየገባ ሲመጣ ልማት ባንኩ በኩባንያው የስራ አመራር ውስጥ እየገባ መጠነኛ ድጋፍ  ያደርግለት ነበር። ይሁንና የጨርቃጨርቅ ኩባንያው የደረሰበት ኪሳራና ቀውስ ማኔጅመንቱን ሙሉ ለሙሉ በባንኩ ስር እንደገባ አስገድዶታል።በተለይ ኩባንያው በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን በስሩ የያዘ መሆኑ ወደዚህ የባሰ ችግር መግባቱ ከባንኩ የተበላሸ ብድር ባሻገር የሚያመጣው ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስም ከባድ በመሆኑ ልማት ባንኩ ውሳኔ ላይ ለመድረስና እርምጃ ለመውሰድ  ተቸግሮ እንደቆየ የልማት ባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል።

Workers at AYKA compound

አይካ አዲስ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲገባ ብዙ ድጋፍ የተደረገለት ነው ።የተሰጠውም ብድር ይህንኑ የድጋፉን ልክ ነው የሚያሳየው።ይህም ብቻ ሳይሆን ችግር ውስጥ ገብቻለሁ በሚልበትም ጊዜ ልማት ባንኩ ከመቶ ሚሊየን ብር በላይ በመስጠት የተለያዩ ወጪዎቹን ተጋርቶታል።ጥሬ ጥጥ ከውጭ ሀገር  ማስገባት በማይፈቀድበት ጊዜ እንኳ በልዩ ሁኔታ ከውጭ እንዲያስገባም ተፈቅዶለት ነበር። ሆኖም ግን ኩባንያው በተቃራኒው በተጋነነ ዋጋ አቅማቸው የተዳከመ ማሽኖችን ያስገባ ነበር ።

አይካ አዲስ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ደረጃ ኪሳራ እያስመዘገበና ብድር መክፈል አቅቶኛል እያለ በቡርኪናፋሶ አዲስ ኢንቨስትመንት ላይ ሊሰማራ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ብዙዎች በሚያስመዘግበው ኪሳራ ተአማኒነት ላይ ጥያቄን እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
ሆኖም አሁን ላይም ቢሆን ኩባንያው በልማት ባንኩ ቁጥጥር ስር መሆኑ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያመጣው ይችላል ወይ የሚለው ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም ባንኩም ራሱ እጅግ በተተበተበ ችግር ውስጥ ያለ በመሆኑ። ከዚህ ቀደም በአዳማ በሌሎች የቱርክ ባለሀብቶች እጅ የነበረውን ኤልሲ አዲስንም ባለሀብቶቹ አንድ ቢሊየን የሚደርስ ብድር ሳይከፍሉ በመጥፋታቸውና ልማት ባንኩ በጨረታ ሊሸጠው ባለመቻሉ እያስተዳደረው ይገኛል።