• ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳ የፓርቲው የፌደራል መንግስት ተሿሚዎች ጉዳይ ግን በይደር እንዲቆይ ተደርጓል

ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ሁለት ቀናት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በድርጅቱ ፅህፈት ቤት ባደረገው ግምገማ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል ያላቸውን የድርጅቱን አመራሮች ከሀላፊነት አግዷል።

በክልል ደረጃ ባሉና በብድር አገልግሎት ሽፋን ከ60 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል የተባሉ ሀላፊዎች ከማናቸውም የድርጅትና የመንግስት ሀላፊነታቸው እንዲታገዱ ተወስኖባቸዋል።  

አቶ ፀጋ አራጌ የተባሉ የፓርቲው የስነምግባርና ቁጥጥር ኮሚሽን ሃላፊ ጉዳዩ ለህዝብ ጆሮ እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ በድርጅቱ ውስጥ የበረታ ጥያቄ ሲብላላ ቆይቷል። 

የተባለውን የገንዘብ ምዝበራ ክስ ተከትሎ  ጉዳዪን የመከረበት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ችግሩ እውነት ሆኖ ስላገኘው ትናንት በአመራሮቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል።

ጉዳዩን የተመለከተው ፓርቲው ገንዘቡን የወሰዱ አመራሮች በድርጅቱ ጉባዔ እንዳይሳተፉ፣ የወሰዱትን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍሉ እና ከስራ እንዲታገዱ ወስኗል። 

ውሳኔው የተላለፈባቸው አመራሮችና ባለሙያዎች  

 • አቶ አማኑዔል ፈረደ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ 3.6 ሚሊዩን ብር ምዝበራ የተወነጀሉ ፣ 
 • አቶ ፍስሃ ደሳለኝ ድርጂት ጉዳይ ኃላፊ 3.8 ሚሊዩን ብር ምዝበራ የተወነጀሉ ፣ 
 • አቶ ጋሻው ተቀባ የወጣቶች ሊግ ሀላፊ 1.8 ሚሊዮን ብር፣ 
 • አቶ ባህሩ ፈጠነ የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ 8.9 ሚሊዮን ብር፣ 
 • ወ/ሮ አዲሴ ቦጋለ የሰው ሀይል መምሪያ ኃላፊ 1.2 ሚሊዮን ብር፣ 
 • ወ/ሮ እየሩስ አባቡ  የንብረት ክፍል ኃላፊ 1.1 ሚሊዮን ብር፣ 
 • አቶ ደሳለኝ በላይ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩ 3 ሚሊዮን ብር፣ 
 • አቶ ጌትነት አይቸው የአማራ ብልፅግና የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ 8.4 ሚሊዮን ብር፣
 • አቶ ፈቃዴ ዳምጤ  የኦዲትና ቁጥጥር ኃላፊ 1.5 ሚሊዮን ብር፤ 
 • አቶ ጌታቸው ብርሃኑ የማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ 1.8 ሚሊዮን ብር፤ 
 • አቶ ጎሹ እንዳላማው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩ 5 ሚሊዮን ብር፤ 
 • አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ም/ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ 3.9 ሚሊዮን ብር፤ 

በባለሙያ ደረጃ

 • ወ/ሮ መሠረት መለሠ ተላላኪ 370,000 ብር፤ 
 • ወ/ሮ ዘነቡ ጋንፉር ገንዘብ ያዥ 550,000 ብር፤ 
 • ወ/ሮ ስራነሽ ዩሀንስ ገንዘብ ያዥ 500,000 ብር ምዝበራ የተወነጀሉ ናቸው።

ውንጀላው የቀረበባቸው ግለሰቦች ገንዘቡን ከነወለዱ ካልመለሱ በአፋጣኝ በህግ የሚጠየቁ መሆናቸውን ፓርቲው አሳስቧል።

እንደምንጮች ገለፃ በፌደራል ደረጃ ባሉ እና ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ስማቸው ስለሚነሱ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ የግምገማ መድረክ ምንም እንዳልተባለ ገልጸው ምናልባትም በአዲስ አበባ በሚደረገው ዋናው የብልጽግና ፓርቲ ግምገማ ላይ ሊነሳ ይችል ይሆናል የሚል ግምት አላቸው።

ትናንት ማምሻውን ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የአማራ ብልፅግና የፌደራል መንግስት ሹም እንደነገሩን ከሆነ ተፈፅሟል በተባለው ምዝበራ ላይ ሰፊና ገለልተኛ ማጣራት ተደርጎ አጥፊዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው። ይሁንና ፓርቲውን ለማዳከምና ለመከፋፈል የተወሰኑ ባለስልጣናትን ስም እያነሱ የሚደረጉ ዘመቻዎች ለህዝብ ከመቆርቆር የሚመነጩ አይደሉም ይላሉ።

“የአማራም ሆነ የየትኛውም ፓርቲ ባለስልጣን ከህግ በላይ አይደለም”  ያሉን ምንጫችን አጠቃላይ ብልፅግና ውስጥ ከኢሕአዴግ ዘመን ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ የሙስና ችግር መኖሩን ያመለክታሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]