Lagarde
IMF Head, Christian Lagarde and PM Hailemariam Desalegn
  • 12 ፋብሪካዎች ምርት አቁመዋል
  • ዶላር በጥቁር ገበያ በድጋሚ አሻቅቧል
  • ባንኮች የደንበኞቻቸውን የቁጠባ ብር ለመስጠት ያንገራግራሉ
  • በመርካቶ የግንባታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል
  • የብረት አምራቾች አኩረፈዋል፡፡ ከአቅም በታች እያመረቱ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በሀገሪቱ መንግስት የጀመራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች በፈጠሩት ከልክ ያለፈ መለጠጥ ከሁሉ በላይ ደግሞ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለው አለመረጋጋት ኢኮኖሚውን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጎታል። ፋብሪካዎች ማምረት አቁመዋል፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት የማያወላዳ ደረጃ ላይ ነው። ነዳጅና መድሀኒትን የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከውጪ ሀገር ለማስገባት በቂ ምንዛሪ በመንግስት ካዝና የለም። ይህ ሁሉ የሚሆነው አንዳንድ አለማቀፍ ተቋማት “አድጓል ተመንድጓል” በሚሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው።
የኢኮኖሚ ቀውሱ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ በተባባሰበት በዚህ ወቅት የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሀላፊ ክርስቲያን ላጋርድ ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል። ላጋርድ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገሪቱ አስቸኳይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንድታደርግ ሀሳብ አቅርበዋል። ለረጅም አመታት ራሴን ከኒዎሊበራል ሀይሎች አላቅቄ በነፃነት አዲስ የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ የኢኮኖሚ ፍልስፍና እከተላለሁ ለሚለው ገዥው ፓርቲ ለአለማቀፉ ሀይላት ማጎብደድን ግድ ብሎታል። የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት በፊናው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመታደግ የገንዘብ ድጋፍ በአፋጣኝ ለማቅረብ መልካም ፈቃዱን አሳይቷል። የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ገፅታ በመጠኑ ካሳየ ብለን ሪፖርተሮቻችን ስሞኑን ያሰባሰቡትን መረጃ አስናድተነዋል። ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ይመልከቱ

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ምንጩ ያልታወቀና ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ መናወዝና የዋጋ ዝብርቅርቅ መከሰቱን በመርካቶ የተዘዋወሩ ዘጋቢዎቻችን ነግረውናል፡፡ ከ12 በላይ የሚስማር የቆርቆሮና የብረታ ብረት አምራች አገር በቀልና አገር ተከል ፋብሪካዎች ምርት በከፊልና ሙሉ በሙሉ ማቆማቸውንም አገር ቤት የሚገኙ ወሬ አቀባዮቻችን ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ይመስላል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ባለፉት አስር ዓመታት ታይቶ ያልታወቀ የዋጋ ጭማሪ በመርካቶ ገበያ ላይ መከሰቱ እየተነገረ ያለው፡፡ በተለይ ጭማሪው የተስተዋለው በግንባታ እቃዎች ላይ መሆኑ ነገሩን እንግዳ አድርጎታል፡፡ በተለምዶ የግንባታ ግብአቶች አንጻራዊ መረጋጋት የሚታይባቸው ናቸው፡፡

ከ32 እስከ 28 ጌጅ የቆርቆሮ ዋጋ ከሦስት መቶ ብር በላይ ማሻቀቡም አዲስ ክስተት ሆኗል፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ልሙጥና ባለ ሀዲድ የጣሪያ ቆርቆሮ ሲያቀርቡ የኖሩት የኻሊፋው ሐዲድ ቆርቆሮ (ሐዲድ ትሬዲንግ)፣ የአዳማ ብረት ፋብሪካ፣ ዲኤች ገዳ ቆርቆሮ፣ ሁለተኛውን ሸራተን እየገነባ የሚገኘው ዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ፣ ኢትዮጵያን ስቲል፣ ብሥራት ቆርቆሮ፣ ሰላም ቆርቆሮና አቃቂ ብረታ ብረት ምርቶቻቸውን በበቂ ማከፋፈል ካቆሙ ሁለት ሳምንታት ያለፋቸው ሲሆን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለትና ከወራት በፊት የአንድ ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ያደረገው የሕንዱ አርቲ ቆርቆሮና ብረት ፋብሪካ ምርት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ማቆሙ ተሰምቷል፡፡ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት ሌላው የአቶ ዮሐንስ ሲሳይ ‹‹የሱ ቆርቆሮ›› ፋብሪካም እንዲሁ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ምርት በከፊል ማቆሙ እየተነገረ ነው፡፡
በተመሳሳይ የውጭ ባለሐብቶች የተከሏቸውና አገር በቀል የብረት አምራቾች ምርታቸውን በቁጠባ እየሸጡ ሲሆን ብረት በከፍተኛ ዋጋ እንኳን ለማግኘት የሳምንታት ወረፋ መያዝ የግድ እየሆነ እንደመጣ ዘጋቢዎቻችን ታዝበዋል፡፡ አቢሲኒያ፣ ዋሊያ፣ ስቲሊ አርኤምአይ፣ኢስት ስቲል፣ ሲኤንድ ኢ ወንድማማቾችና ሌሎች ከአስራ አንድ በላይ የብረት አምራቾች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋጋ እንዲያስተካክሉ ከተነገራቸው በኋላ ምርታቸውን በግማሽ መቀነሳቸው ተሰምቷል፡፡ የአምራቾቹ የዋጋ ቅሬታ ከውጭ ምንዛሬ እጦት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የዋጋ ዝብርቅርቅ እንደፈጠረ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት የተደረገውን የዶላር ዋጋ ማስተካከያ ተከትሎ ብረት ነጋዴዎች የ39 በመቶ ድንገተኛና ምክንያት የለሽ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ለፓርላማ አስረድተው በአስቸኳይ ዋጋ ካላስተካከሉ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተው ነበር፡፡ ይህንኑ ዛቻቸውን ተከትሎ ነው የምርት ድርቅ የተከሰተው፡፡
ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ምናልባት አስመጪ ነጋዴዎች በባንክ ሲያካሄዱት የነበረው ከኢንቮይስ በታች (under invoice) ዘዴ በብሔራዊ ባንክ በኩል እንዲቆም መደረጉ የሌሎች የግንባታ ግብአቶችን ዋጋ ንረት ሳይፈጥረው እንዳልቀረ ይነገራል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረ የዘተለምዶ አሰራር አንድ አስመጪ የ5ሺ ዶላር ከኢትዮጵያ ባንክ በሕጋዊ መንገድ አስፈቅዶ ወደ አገር ዉስጥ የሚያስገባው ግን ከአምስት መቶ ሺህ ዶላር የሚልቅ ዕቃ ሊሆን ይችላል፡፡ ቀሪውን ገንዘብ ከውጭ በሀዋላ በኢመደበኛ መንገድ ተከፋይ በማድረግ ገቢ እቃዎች መንግስት ካወጣላቸው የሲዲ ዋጋ በተለየ እንደመጡ ተደርጎ ይሰላ ነበር፡፡ በቅርቡ ይህ አሰራር ወደ መደበኛ የሲዲ ዋጋ መዛወሩ በርካታ አስመጪዎችን ከጨወታ ውጭ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡ ይህ አሰራር ከፍተኛ ባለሐብቶችና በመንግሥት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ነጋዴዎችን ብቻ ለመጥቀም የተመቸ አድርጎታል ይላሉ ለዘጋቢዎቻችን አስተያየታቸውን የሰጡ አስመጪዎች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሌላው አዲስ ክስተት የሆነው ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚከፍሉት ብር እያጡ መምጣታቸው ነው፡፡ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በአንድ ጊዜ ወጪ ለማድረግ የግልም ባንኮችም ሆኑ ንግድ ባንክ ፍቃደኞች እንዳልሆኑ የተናገሩ በጆንያ ተራ የጅምላ ነጋዴ ‹‹የገዛ ብራችንን ታግቶብን የባንክ ማኔጀሮችን የምንለማመጥበት ጊዜ ላይ ደርሰናል›› ይላሉ፡፡
የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገንዘብ እጥረት እንደገጠማቸውና ደንበኞች በአንድ ጊዜ ከፍ ያለ ብር ሲጠይቁ ጥያቄያቸውን በፍጥነት ለማስተናገድ መቸገራቸውን ይናገራሉ፡፡ በመርካቶ የአዋሽ ባንክ ባንክ ኦፊሰር ‹‹ይህ ሁልጊዜ የሚገጥም ነገር አይደለም፤ በተቻለ መጠን ገንዘቡን አሰባስበን ከሦስት ቀናት ባልበለጠ ለደንበኞች እንከፍላለን›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የችግሩን ምክንያት ተጠይቆ- አለመረጋጋት ሲከሰት ዜጎች ብሮቻቸውን ከባንክ ያወጣሉ፣ በርካታ ደንበኞቻችንን ንግድ ባንክ ወስዶብናል…ገንዘብ እጥረቱ ግን አሁንም ቢሆን ጊዝያዊ ችግር ነው›› ብሏል፡፡
ዶላር በጥቁር ገበያ በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ የ80 ሳንቲም ጭማሪ እንዳሳየም ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ አንድ ዶላር በ31 ብር ከ80 ሳንቲም እየተገዛ ይገኛል፡፡

https://youtu.be/hNrJx7z9avc