Nalbandian during 1950's performance with one of the famous band at the time
Nalbandian during 1950’s performance with one of the famous band at the time

ዋዜማ ራዲዮ- ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ መዳበር ባደረጉት አስተዋፃኦ የሚታወቁት አርመናዊው ነርሲስ ናልባንዲያን የመታሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ተደረገላቸው። በሳምንቱ መጨረሻ በዩናይትድስቴትስ በማሳቹሴትስ ግዛት ዋተርታውን ከተማ የተደረገውን የሙዚቃ ኮንሰርት በርካታ የሙዚቃ አፍቃርያን ኢትዮጵያውያንና አርመናውያን ታድመውታል።የናልባንድያን ቤተሰቦችም ተገኝተዋል።

መቀመጫውን ቦስተን ያደረገው ኢዘር ኦርኬስትራ(Either Orchestra) የነርሲስ ናልባንዲያን ስራዎችን አቀናብሮ ለተመልካች አቅርቧል። ኢዘር ኦርኬስትራ ሙሉ በሙሉ የውጪ ሀገር ባለሙያዎችን የያዘና ከአስር አመታት ወዲህ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች በመላው አለም እያቀረበ የሚገኝ ቡድን ነው። ከዚህ ቀደም አንድ የሙዚቃ አልበም ለታዳሚ ያቀረበ ሲሆን በአዲስ አበባም ኮንሰርቶችን በማቅረብ እንግዳ አይደለም።

በማሳቹሴትስ በተደረገው የናልባንዲያን መታሰቢያ ላይ የነርሲስ ናልባንዲያን ቅንብሮች የቀረቡ ሲሆን ስራዎቹ በቅርቡ በአልበም መልክ ለሙዚቃ ወዳጆች እንደሚቀርቡ ታውቋል። አልበሙ ኢቶፒከስ በሚል በተለያዩ ቅፆች ከቀረቡት ከሀያ በላይ አልበሞች ውስጥ አንዱ ይሆናል። የደቦ ባንድ ድምፃዊ ብሩክ ተስፋዬ የአማርኛ ዜማ የተጫወተ ሲሆን የእንግሊዘኛ ስፓኒሽና አርመን ቋንቋ ዜማዎችም ቀርበዋል።

ነርሲስ ናልባንዲያን በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1940 እስከ 1970 ድረስ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ከበሬታን ያሰገኘላቸውን የሙዚቃ ቡድን የማቋቋም ሙዚቀኞችን የማሰልጠን ና የማቀናበር ስራ በመስራት ለዘመናዊው ሙዚቃ ማደግ የላቀ አስተዋፃኦ አድርገዋል። ናልባንድያን  በአርመንያ ከነበረው የዘር ፍጅት ሸሽተው በእስራኤል በማደጎነት ሲኖሩ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ናልባንድያንን ጨምሮ አርባ ታዳጊዎችን በ1924 በማደጎ ተረክበው በማሳዳግ ለወግ እንዳበቋቸው የታሪክ ድርሳናቸው ይናገራል። ነርሲስ ናልባንድያን የኢትዮጵያ ዜግነት የነበራቸው ሲሆን በ1969 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ ህይወታቸው አልፏል።