የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውቅታዊ ሁኔታዎችን ከገመገመ በኋላ ምክትል ከንቲባና ታከለ ኡማና ሌሎች አመራሮች ከስልጣን እንዲነሱ የተደረሰበትን ውሳኔ ቀልብሶታል። ቢሯቸውን ለመልቀቅና ለትምህርት ወደ ውጪ ለመሄድ ሲሰናዱ የነበሩት ታከለ ኡማ የውሳኔውን መሻር ተከትሎ የከተማውን ካቢኔ ስብስበው ስለሁኔታው አስረድተዋል። ዋዜማ መረጃውን ተከታትላለች። አንብቡት

D/Mayor Takele Uma- Photo credit- Mayor office

ዋዜማ ራዲዮ- ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ኦዴፓ ) ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን ውሳኔ ተከትሎ ትላንት (አርብ) የካቢኔ አባሎቻቸውን ሰብስበው እንደነበር ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ማረጋገጥ ችላለች።

በዚሁ ስብሰባ ላይ ምክትል ከንቲባ ታከለ ለካቢኒ አባሎቻቸው እሳቸውና ሌሎች ከፍተኛ ሹመኞች ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርሶ የነበረው ውሳኔ እንደተሻረ ነግረዋቸዋል። ከሀላፊነት የመነሳት ውሳኔው የቀረው ለጊዜው ነው ? ላልተወሰነ ጊዜ ነው? ወይስ በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እስኪካሄድ ነው? የሚለው ግን አልተገለጸም።

 በከተማዋ ከፍተኛ ሹሞች በተይም በታከለ ኡማ እና በማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪው እንዳወቅ አብጤ መካከል የነበረ አለመተመማንና “መሳሳብ” ምክንያት በተፈጠረ ችግር ምክንያት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የመከላከያ ለማ መገርሳ በተገኙበት በተደረገ ግምገማ ምክትል ከንቲባዎቹ ከሀላፊነት እንዲነሱ መወሰኑን ዋዜማ ራዲዮ መዘገቧ ይታወሳል

ከሀላፊነት ይነሳሉ ተብሎ የነበረው ምክትል ከንቲባዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊው ተስፋዬ በልጅጌ እና የአዲስ አበባ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ : (አዴፓ) : ጽህፈት ቤት ሀላፊ ጸጋ አራጌ እንዲሁም የከተማው ስራ አስኪያጅ አወቀ ሀይለማርያም ነበሩ።

ሆኖም ውሳኔም እንዲቀለበስ ያደረጉ ሁለት ምክንያቶችም ተነስተዋል።

የስልጣን ሽኩቻ የኢህአዴግን ውህደት ያሰናክላል

አንዱ በከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ቢሮ ሀላፊ እንዳወቅ አብጤ መሀከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች መነሻ በዋናነት ; ሁለቱ ምክትል ከንቲባዎች የተወከሉበት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) አባላት የከተማው የስልጣን ክፍፍል ኢ-ፍትሀዊነት ጥያቄ ነው ።

ሁለቱ ፓርቲዎች ደግሞ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ለማምጣት እየታሰበ ባለው ውህድ ፓርቲ አማካይነት ህልውናቸው ከስሞ ለመታቀፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይህ የማዋሀድ ጥረት የሚሳካ ከሆነ ደግሞ የከተማው የስልጣን ክፍፍል ላይ የኦዴፓና አዴፓ ፓርቲ አባል በሚል የሚፈጠር መሳሳብ ይቀራል ተብሎ ስለሚታሰብ የውህደቱ ሁኔታ እስኪለይ ከተማውን ተስማምተው ይምሩ የሚለው ነው። በዚህ ሰአት እንዲህ አይነት ሹም ሽር ማካሄድም ለውህደቱ ችግር እንዳይሆን ተስግቷል።

ክፍተቱን ለመጠቀምና መንግስት ላይ ለማመፅ ያደፈጠ ሀይል አለ

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ሌሎች ሹሞች ይነሳሉ ተብሎ መወሰኑን ተከትሎ ውሳኔውን ለድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም ያኮበኮበ ሀይል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል የሚል ስጋት መንግስትን እንዳሳሰበው ተሰምቷል። ሆኖም ይህ የተባለው ሀይል ማን እንደሆነ ግን አልተብራራም ። ታከለ ኡማም በካቢኒው ስብሰባ ላይ ይህን በግልጽ አላብራሩም።

ምክትል ከንቲባውና ሌሎቹ ሹሞች ከሀላፊነት ከተነሱ በሁዋላ ለትምህርት አሜሪካ እንደሚሄዱም ተነግሯቸው እንደነበር ማረጋገጥ ችለናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች ከሀላፊነት እንዲነሱ በጋራ ውሳኔ አስተላልፎ የነበረው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም። የውሳኔው መሻር የሁለቱ የጋራ ድርጅቶች ስምምነት ይሁን የተናጠል ዋዜማ ማረጋገጥ አልቻለችም።