ዋዜማ ራዲዮ- ከ7 ወራት መዘግየት በኋላ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አብዲ ሞሀመድ (አብዲ ኢሌ) ላይ ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ለመጀመርያ ጊዜ ምስክር መሰማት ተጀመረ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገመንግስት እና የፀረሽብር ጉዳዮች ችሎት የካቲት 26 ቀን 2012 ዓም በተሰየመበት ወቅት አቃቤ ህግ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ ሞሀመድ እና ሌሎች በመዝገቡ በተካተቱ ተከሳሾች ላይ አለኝ ያላቸውን ምስክሮች ከሚያዝያ 15 2012 ዓም ጀምሮ በችሎት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ሁሉም ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት ወር ጀምሮ ጉዳዮችን ማስተናገድ በማቋረጣቸው ይሄ መዝገብ ዘግይቶ ቆይቷል፡፡

ታዲያ ዛሬ ከ7 ወራት በኋላ በችሎት በቀረቡት ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ የመጀመርያ ምስክሩን አቅርቧል፡፡ በቀጣይ ቀናትም ምስክሮቹን ማሰማት እንዲቀጥል ቀጠሮ ተይዟል

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥር 20 2011 ዓም በመሰረተው ክስ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 47 ግለሰቦች በክልሉ በተለያዩ ስብሰባዎች እና በፌስቡክ ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት አብያተ ክርስትያናት መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]