Tesfaye Gessesse
Tesfaye Gessesse

 

ዋዜማ ራዲዮ- 80ኛ ዓመታቸውን ባለፈው ሰሞን፣ መስከረም 17 የደፈኑት አንጋፋው የኪነ ጥበብ ሰው ተስፋዬ ገሠሠ ልደታቸውን አስታከው 763 ገጽ ያለው መጽሐፍ አስመርቀዋል፡፡ መጽሐፉ “A Long Walk to Freedom” የተሰኘው የደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ ቆየት ያለ መጽሐፍ የአማርኛ ትርጉም ሲሆን በ200 ብር ለአንባቢ ቀርቧል፡፡

በቼምበር ማተሚያ ቤት የታተመው ይህ የትርጉም ሥራ ለረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ 8ኛው የሕትመት ሥራቸው ነው፡፡ “መተከዣ” የአጫጭር ግጥሞችና ልቦለዶች ስብስ፣ “መልከአ ኡመር” (ተዛማጅ የግጥም ትርጉም)፣ “የዑመር ኻያም የሕይወት ታሪክና ሥራዎቹ” ትርጉም፣ “ጎህ ሲቀድ” (የግጥም መድብል)፣ እና “ሽልማቱ” የተሰኘ ሌላ አወዛጋቢ ልቦለድ ከሕትመት ሥራዎቻቸው የሚጠቀሱላቸው ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ በተገኙበት የልደት በዓላቸው ለረዥም ጊዜ በኃላፊነት የሰሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባሕል ማዕከል የተከበረ ሲሆን ከእንግዲህ ማዕከሉ “ተስፋዬ ገሠሠ የባሕል ማዕከል” ተብሎ እንዲጠራ የሴኔት ዉሳኔ አግኝቷል ተብሏል፡፡

የመጨረሻው የትርጉም ሥራቸው የኔልሰን ማንዴላ ግለ ታሪክ የፊት ገጽ ሽፋኑ ማንዴላ በ1991 ዓ. ም በሮብን ደሴት እየተራመዱ የሚያሳይ ሲሆን የጀርባ ሽፋኑ የማንዴላ ኦፊሴል ፖርትሬት ፎቶ ያጌጠ ነው፡፡

የትርጉም ሥራው በ11 ምዕራፎች የተሸነሸነ ሲሆን ክፍል አንድ የማንዴላን በገጠር ያሳለፉትን የሕጻንነት ዘመን ይዳስሳል፡፡ በክፍል 10 ከጠላቶቻቸው ጋር ያደረጉትን ድርድር የሚዳስስ ኾኖ በመጨረሻው የመጽሐፉ 11ኛ ምዕራፍ የነጻነት መቀዳጀትን ጉዳይ ያወሳል፡፡

የትርጉም ሥራው ምንም አይነት መቅድም፣ መግቢያ፣ ወይም የተርጓሚው ማስታወሻ ያልተበጀለት ሲሆን የምዕራፍ ማውጫንም አላካተተም፡፡

ተስፋዬ ገሠሠ በብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅነትና በአገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪያጅነት ለዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከብሔራዊ ቴአትር ወደ ቴሌቪዥን ተዛውረው አስተዋዋቂና የትርፍ ጊዜ ጋዜጠኛ ሆነውም አገልግለዋል፡፡፡፡

ወደ ኪነጥበብ ዓለም የተቀላቀሉት በ1940ዎቹ መጨረሻ ሲሆን የ4ኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ለምረቃ ፕሮግራም “እዮብ” የተባለ ቴአትር ተዘጋጅት ስለነበር በዚያው ሰሞን ተከፍቶ በነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአተር ቤት ዉስጥ ይኸው ተውኔት ማታየቱን ተከትሎ ነው ወደ ጥበብ መስመር የገቡት፡፡ በተውኔቱ መሪ ተዋናይ እዮብን ሆነው የተጫወቱት ተስፋዬ ገሠሠ ነበሩ፡፡

በአጋጣሚ ንጉሡ ይህን ቴአትር ተመልክተው ስለወደዱት ተስፋዬ ገሠሠን ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት እንዳስጠሯቸውና ከረዳታቸው ከልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጋር አብረው እንዳነጋገሯቸው ይወሳል፡፡ በወቅቱ የትምህርት ዝንባሌያቸውና ወደፊት መሆን የሚፈልጉትን እንዲያስረዱ በንጉሡ የተጠየቁት ተስፋዬ ገሠሠ ሕግ ማጥናት እንደሚፈልጉ ቢናገሩም በወቅቱ 12 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በዉጭ አገር ሕግ እየተማሩ ስለበር ‹‹የሕግ ሰው ይበዛብናል፣ አንተ መማር ያለብህ ቴአትር ጥበብ ነው›› ብለው ንጉሡ እንደወሰኑላቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት ልጅ እንዳልካቸው ተጻጽፈው ወደ ኒውዮርክ ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርስቲ እንደላኳቸውና እዚያም የቴአተር ጥበብ እንዳጠኑ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

‹‹ጃንሆይ በኔ ላይ ትልቅ የሕይወት ለውጥ ነው ያደረጉት›› ሲሉ ለዶቼቬሌ በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡

30 ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ አሁን በቴአትር ዓለም ላይ የሚገኙትን አንጋፋ ተዋናዮችን አስተምረዋል፡፡ በመድረኩ ዓለም በስፋት የሚታወቁት ፀጋዬ ገብረመድህን ባዘጋጃቸው ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ነው፡፡ የእሾህ አክሊል፣ ሐምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ የመንግሥቱ ለማን ባለ ካባና ባለ ዳባ አዘጋጅተዋል፣ ተውነዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ጡረታ ከወጡ በኋላም ቢሆን በጥቂት ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ አልፎ አልፎ ብቅ ይላሉ፡፡

ተስፋዬ ገሠሠ የተወለዱት በ1929 ዓ.ም ነው፡፡ የትውልድ ቀያቸው ሐረርጌ ጎሩ ጎቱ ወረዳ፣ ደደር ከሚባል ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኝ የገጠር ቀበሌ ናት፡፡ ለ20 ዓመት ከመጀመርያዋ ባለቤታቸው ጋር፣ እንዲሁም ለ30 ዓመታት ከሁለተኛዋ ባለቤታቸው ጋር በቆዩበት የ50 ዓመታት የትዳር ሕይወታቸው 5 ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን እንዳፈሩም ይነገራል፡፡