Yinager Dessie, Chief of NBE

ዋዜማ ራዲዮ – የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአዲሱ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ መመራት ከጀመረ በሁዋላ የፋይናንሱ ዘርፍ ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ነው።ዋዜማ ራዲዮ ከሳምንታት በፊት እንደዘገበችው ብሄራዊ ባንኩ ለተበዳሪዎች የብድር መክፈያ ጊዜን ከማራዘም አንጻር አዲስ መመሪያን አውጥቶ ለሀገሪቱ ንግድ ባንኮች በሙሉ አሰራጭቷል።አሁን ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ሀገር ገበያ የሚልኩ ኤክስፖርተሮች ሀገር ውስጥ ያስገቡትን የውጭ ምንዛሬን የሚጠቀሙበትን መመሪያ ሊያሻሽል ስለመሆኑ ከባንክ ምንጮቻችን ሰምተናል።

አሁን ድረስ ጥቅም ላይ ያለው ምርት ላኪዎች ሀገር ውስጥ ያስገቡትን የውጭ ምንዛሬ የሚጠቀሙበት መመሪያ ወይንም :National Bank Export retention policy : ላኪዎችን እጅግ የሚያስጨንቅና የማያበረታታ መሆኑ ብሄራዊ ባንክ ከባለሀብቶች ጋር በሚያደርገው ስብሰባ ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል።

የነባሩ ፖሊሲ ይዘትም ይህ ነው።
አንድ ኤክስፖርተር ወይንም ላኪ ምርቱን ለውጭ ገበያ አቅርቦ በሚጠቀመው የሀገር ባንክ የውጭ ምንዛሬው ሲመጣለት : ከመጣለት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን ሌላ እቃን ለማምጣት በአንድ ወር ውስጥ የግድ ሊጠቀመው ይገባል።የሚያስመጣው እቃም ከሚልከው ምርት ጋር ተያያዥነት ያለው እንዲሆን ያዛል። ላኪው ያስመጣውን የውጭ ምንዛሬ ሰባ በመቶውን በዚህ መልኩ በአንድ ወር ውስጥ ምርቱን ልኮ ያስመጣው የውጭ ምንዛሬ ካልተጠቀመበት በኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ ነው የሚሰጠው። ቀሪው ሰላሳ በመቶ የውጭ ምንዛሬ ነው ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ የሚችለው። ይህ የላኪዎች የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም አሰራር በብዙ መለኪያ ለባለሀብቶች አክሳሪ መሆኑ ይነገራል።

ሲጀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሎጂስቲክስ አገልግሎት አንድ ላኪ ለሀገር ገቢ ያደረገውን ምንዛሬ 70 በመቶ በአንድ ወር ውስጥ ተጠቅሞ ሊጨርሰው አይችልም።ይህም ምንዛሬው ባንኮች ጋር ቀርቶ ላኪዎች ያስመጡትን የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛውን ድርሻ ሳይጠቀሙበት ከእጃቸው ላይ እንዲወጣ የሚያደርግ በመሆኑ ብዙዎችን ደስተኛ አላደረገም።

ከዚህ በላይ የከፋው ነገር ደግሞ ላኪዎች ለሀገር ያስገቡትን የውጭ ምንዛሬ መጠቀም ያለባቸው ከሚልኩት ምርት ጋር ተዛማጅነት ላለው ግብአት እንዲሆን መገደዳቸው ነው።ቡና የሚልክ ግለሰብ ለሀገር ባስገባው የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ገዝቶ ማስገባት የሚችለው ጆንያና ቡና ማጠቢያ ማሽን መሰል ምርቶችን ብቻ መሆን አለበት እንደማለት ነው። ያውም 70 በመቶውን በአንድ ወር ጊዜ መጠቀም ይኖርባቸዋል (በኢትዮጵያ ብር ከመቀየር ለማትረፍ)። ይህም ባለሀብቶች ራሳቸው ባመጡት የውጭ ምንዛሬ ምርጫቸውን ያጠበበ ነው።

በዚህ አሰራር ምክንያት በርካታ ላኪዎች ራሳቸውን ከውጭ ገበያ በማግል የሀገር ውስጥ ንግድ ላይ ለማተኮር ተገደዋል።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ላኪዎች ትርፍን ብዙ ጊዜ የሚያገኙት ከላኩት ምርት ሳይሆን ምርትን ልከው በሚመጣላቸው የውጭ ምንዛሬ እንደገና ሸቀጦችን ከሌላ ሀገር በማስገባት ነበር በቀድሞው ጊዜ።የውጭ ምንዛሬዋን ለማግኘት ብቻ ላኪዎች ቡናን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከገዙበት ዋጋ በታች ውጭ ሀገር ሲሸጡ በተደጋጋሚ ሲታይ ነበር።በረከሰ ዋጋ የመሸጡ አዝማሚያ የመጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከሎጂስቲክስም አንጻር ውድ ስለሆነም ጭምር ነው።ይህች የባለ ሀብቶች ኪሳራ ትካካስ የነበረው ቡናን ልከው ውጭ ምንዛሬ ስለሚያመጡ ብቻ ባንኮች ምንዛሬ ለፈለጉት አላማ ስለሚፈቅዱላቸው ቻይናን ከመሰሉ ሀገራት ሌሎች ሸቀጦችን በማምጣት ዳጎስ ያለ ትርፍን በማግኘት ነው።ይህ አይነቱ አሰራር ከአመታት በፊት እንዲቀር ከተደረገ በሁዋላ ግን ላኪዎች መበረታታት አቁመዋል።

አዲሱ መመሪያ ምን ይዟል?

በዚህ ምክንያት ምርት ላኪ የባንክ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።ነገሩየውጭ ምንዛሬ ፈላጊዎችም ከህጋዊ መንገድ ይልቅ ጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ ካደረጉ አሰራሮች አንዱ ይህ መመሪያ ይህ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለኤክስፖርት ዘርፍ ራስ ምታት በመሆኑም ብሄራዊ ባንክ አሰራሩን ላላ ለማድረግ መወሰኑን ሰምተናል። አዲስ አሰራር ለማውጣት የሚያግዘውን መመሪያ ለማውጣትም ከንግድ ባንኮች መረጃን ሰብስቧል።

አዲሱ የላኪዎች የውጭ ምንዛሬ አጠቃም ህግ ላኪዎች ሀገር ውስጥ የሚያመጡትን የውጭ ምንዛሬን ለሚፈልጉት ምርት ማስመጫነት እንዲጠቀሙ እንዲያስችል ሆኖ እንደሚወጣ ከብሄራዊ ባንክ ሰምተናል። እንዲሁም ላኪዎች ካመጡት የውጭ ምንዛሬ በባንክ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሳይቀየር ለፈለጉት ጊዜ የሚቀመጥላቸውን መጠን አሁን ካለው 30 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ይጠበቃል።በጉዳዩ ላይ ብሄራዊ ባንክ ብዙ ስራዎችን እንዳጠናቀቀና በቅርቡም ወደ ተግባር ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]