National Bank of Ethiopia- FILE

ዋዜማ ራዲዮ – ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ብሔራዊ ባንክ ከአሜሪካ ዶላር አንፃር የብርን የምንዛሪ ተመን የሚያዳክምበትን መጠን ጋብ አድርጎታል። ይህ የብርን ተመን የማዳከም እርምጃ የጠቅላይ ሚንስትሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንድ አካል ነው። አሁን የምንዛሪ ተመን ላይ የታየው ለውጥ የፖሊሲ ውሳኔ  እንደሆነ ብለን ያሰባሰብነውን መረጃ እንደሚከተለው አስናድተነዋል።

ከ2012 አ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያን ብር ከንግድ ሸሪክ ሀገራት መገበያያ አንጻር  በከፍተኛ ደረጃ ሲያዳክም ቆይቷል። ለአብነትም አንድ የአሜሪካ ዶላር በባንኮች የሚሸጥና የሚገዛበት ዋጋ በየእለቱ ከአራት እስከ ስድስት ሳንቲም ጭማሬን ሲያሳይ ቆይቶ የአንድ የአሜሪካ ዶላር መሸጫ ይህን ዘገባ እስከሰራንበት ሰኞ የካቲት29/2014 ዓ.ም ድረስ 50 ብር ከ81 ሳንቲም ደርሷል ።

የወጪ ንግድን ለማሳደግ እንዲረዳ ታስቦ ከለውጡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ እርምጃ ሆኖ የተጀመረው ይህ እርምጃ የታሰበውን ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። 

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዋዜማ ራዲዮ በደረገችው ምልከታ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በብር እና በአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ተመን ላይ የተለየ አካሄድ የተከተለ ይመስላል። ከየካቲት 15 እስከ 29 2014  ዓ.ም ድረስ ባደረግነው ፍተሻ አንድ የአሜሪካ ዶላር  መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ በእየእለቱ እየታየ ያለው ጭማሪ የአንድ ሳምቲም ብቻ ሆኗል። 

ከዚህ ቀደም ከነበረው የአራትና ስድስት ሳንቲም ልዩነት እንዲሁም ካለፉት ሁለት አመታት አንጻርም የየእለት ጭማሬው ቅናሽን አሳይቷል።

በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በአንድ የአሜሪካ ዶላር ላይ አንድ ብር ለመጨመር አሁን ሲወስድ ከነበረው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ከሶስት ወር በላይ እንዲያልፍ ያደርገዋል። በዩሮ እና ፓውንድ ስተርሊንግን በመሰሉት ገንዘቦች ላይ ግን የታየ ለውጥ የለም። ሆኖም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይም ሆነ የውጭ እዳ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የአሜሪካ ዶላር ነው። 

የሁለት ሳምንታት የምንዛሪ ተመን ዝግ ማለት የታሰበበት የፖሊሲ ለውጥ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ አልቻልንም። 

ባለሙያዎች ደግሞ እንዲህ ይላሉ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ብሄራዊ ባንክ በ”ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ” የተከተልኩት የምንዛሬ ፖሊሲ አዋጭ ነበር ወይንስ አይደለም የሚል ዳሰሳ አድርጌ ውሳኔ አሳልፋለሁ ማለቱን ዋዜማ ራዲዮ መዘገቧ ይታወሳል

ከሰሞኑ የታየው ለውጥስ የዚህ ዳሰሳ ውጤት ነው ወይ ስንል አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ነገር ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምንጫችንን ጠቀናል። ምንጫችን እንዳሉን ; ከአጠቃላይ “የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ” አንጻር መንግስት ለውጥ አድርጓል ማለት እንደማይቻል ; ነገር ግን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ስራ ላይ ባለው የምንዛሬ ተመን አሰራር ዙርያ ለመንግስት በኢኮኖሚ ዙርያ በሚሰሩ አማካሪዎች ዘንድ ልዩነቶች እንዳሉ እንደሚያውቁ ነግረውናል።

የተወሰኑት ብርን ማዳከም የወጪ ንግድን ከማሳደግ ይልቅ የዋጋ ንረትን አስከትሏል የሚል አቋም ሲኖራቸው ሌሎቹና በብዛት ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የመጡ አማካሪዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ንረት የተፈጠረው አለማቀፍ ገበያ ላይ በተፈጠረው የዋጋ ንረትና በሀገር ውስጥ ባለ ያለመረጋጋት ነው የሚል አቋም አላቸው ብለውናል ምንጫችን። 

ከዚህ ሁኔታ አንጻር አሁን ላይ መንግስት የፖሊሲ ለውጥ አድርጎ ነው ለማለት እንደሚከብድ ፣ ነገር ግን በአሜሪካ ዶላር ላይ እየታየ ላለው አንጻራዊ ለውጥ የምንዛሬ ተመኑ ራሱ መንግስት ላይ ጫና  በማሳረፉ የመጣ እንደሆነ እንደሚያምኑ ነግረውናል።

“የኢትዮጵያ መንግስት የ”ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ” ቀርጾ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በፍጥነት ማዳከም ሲጀምር ብር በመዳከሙ ሳቢያ የሚፈጠር የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ መናጋትን የሚያካክስ የውጭ ምንዛሬን ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም( አይኤምኤፍ) ; አለም ባንክና ሌሎች ተቋማት እስከ 10 ቢሊየን ዶላር ብድር እንደሚያገኝ ቃል ተገብቶለት ነው። 

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከምዕራቡ አለም ሀገራት ጋር በገባው ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ምክንያት አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ቃል በገቡት መሰረት በወቅቱ አልሰጡም።

የኢትዮጵያ መንግስት ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል ባንኮች ከሚያገኙት ምንዛሬ 70 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንዲሸጡ እስከማዘዝ እንዳደረሰው የሚታወስ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]