ዋዜማ ራዲዮ- ህወሀት ብቻ ሲቀር ሶስት የቀድሞው ኢህአዴግ አባል ፓርቲዎችና አጋሮች በጋራ የመሰረቱት ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ ግዙፍ የተባለ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚያካሂድ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። በቅዳሜው መርሀ ግብር ላይ እንዲሳተፉም በርካቶች ጥሪ ተደርጎላቸዋል።


ባለሀብቶች : ምሁራንና የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙም ተረድተናል። የቅዳሜው የሚሊኒየም አዳራሽ መርሀ ግብርም “የብልጽግና ፓርቲ የማጠናከሪያ ድጋፍ ማሰባሰቢያ የመጀመርያው ምእራፍ ማብሰሪያ የእራት ግብዣ” የሚል ስያሜ ያለው ነው።


በቅዳሜው የእራት ግብዣ ላይ ለብልጽግና ፓርቲ በይፋ ገንዘብ የማሰባሰብ መርሀ ግብር የማከናወን እቅድ ይኑር አይኑ መረጃ ማግኘት አልቻልንም። ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጀምሮ ከባንኮችና ኢንሹራንሶች ፣ከንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እየሰራ እንደሆነ ይነገራል። በአዲስ አበባ ከተለያዩ አካላት የድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰቡን ተረድተናል።
ለምርጫ ዘመቻ የፖለቲካ ስራ ገንዘብን በተለያየ መልኩ በድጋፍ ማሰባሰብ በሌሎች ባደጉ ሀገራት የተለመደ ቢሆንም አሁን በብልጽግና ፓርቲ በኩል እየተደረጉ ያሉ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራዎች ግን በተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጫና በመፍጠር የተከናወኑ ናቸው በሚል ከዚህ ከዚያም ወቀሳዎች ይደመጣሉ።
የቅዳሜው የፓርቲው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብርም በአይነቱ ለየት ያለ እንደሆነ ተነግሮለታል። [ዋዜማ ራዲዮ]