በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የሕወሐት አባላት ብልፅግና ፓርቲን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸው በጎ ምላሽ የሰጡ በርካቶች ናቸው። ብልፅግና ፓርቲን በመቀላቀል ከህወሐት የሚደርስባቸውን ጫና ግን ከወዲሁ ፈርተውታል። ዝርዝሩን ያንብቡት

ዋዜማ ራዲዮ – የኢትዮጵያ ገዥ ግንባር ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እህት ድርጅቶቹን አክስሞ እና አምስት አጋር ድርጅቶችን ቀላቅሎ ብልጽግና ፓርቲን የመመስረቱ ሂደት ቀና መንገድ ላይ እንደሆነለት እየገለፀ ነው።

ከአራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ሶስቱ ውስጥ ለውስጥ የሚነሱ ቅራኔዎቻቸው እንዳሉ ሆነው ከሞላ ጎደል በሚመሰረተው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ከስመው ለመዋሀድ ተስማምተዋል። አምስቱ አጋር ድርጅቶችም እንዲሁ የብልጽግና ፓርቲ አካል ለመሆን ስምምነታቸውን ገልጸዋል።

የውህድ ፓርቲው አባል ለመሆን ፍላጎት አለማሳየት ብቻም ሳይሆን ግልጽ ተቃውሞውን በብልጽግና ፓርቲ ላይ እያንጸባረቀ ያለው ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ነው። ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉም ሆነው ውህድ ፓርቲው ህወሀትን እና የፌዴራል መንግስትን ይበልጥ አቃቅሯቸዋል።


ሆኖም በአዲስ አበባ የኢህአዴግ አደረጃጀት ውስጥ ሆነው ውክልናቸው ወይንም እናት ድርጅታቸው ህወሃት የሆኑ አባላት ከእናት ድርጅታቸው ወጥተው የብልጽግና ፓርቲ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች ካሉ አዲሱ ውህድ ፓርቲ በአባልነት ሊቀበላቸው ዝግጁ መሆኑ እንደተገለጸላቸው ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መረዳት ችላለች። እናት ድርጅታቸው ህወሀት ለሆኑና በአዲስ አበባ ከተማ የኢህአዴግ አደረጃጀት ውስጥ ለቆዩ አባትም ይህ አማራጭ በተደጋጋሚ ቀርቦላቸዋል።


ዋዜማ ራዲዮ መረዳት እንደቻለችው በአዲስ አበባ ያሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የህወሀት አባላት በግለሰብ ደረጃ የብልጽግና አባል የመሆን ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን የፓርቲው አባል መሆናቸውን ተከትሎ ሊከሰትባቸው የሚችለውን ጫና በመፍራት ፈጣን ውሳኔን ለማስተላፍ እንደተቸገሩም ነው የሰማነው።

በርካቶቹ የሕወሐት አባላት በአዲስ አበባ በከተማና በፌደራል መንግስት መዋቅር ውስጥ በተለያየ የሀላፊነት ደረጃ እየሰሩ ያሉ ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]