Attorney General Gedion Timotiwos —Photo AFP

ዋዜማራዲዮበአገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበውን ‹አካታች› አገራዊ ምክክር በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር ሊመሰረት የታቀደው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የኮሚሽነሮች አወቃቀርና አደረጃጀት ከአስፈጻሚው የመንግስት አካል ነጻ ሆኖ እንዲቆም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የዲሞክራሲ ተቋማት ጠየቁ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ 1/2014 ዓ/ም ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም በሚል በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ተወያይቶበት ለዝርዝር አይታ ለምክርቤቱ የለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡

የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበው ቋሚ ኮሚቴው በረቂቁ ላይ ወይይት ሲያደርግ ከቆየ በኃላ በረቂቅ አዋጁ ላይ  ሰኞ ታህሳስ 11ቀን 2014 ዓ.ም የሕዝብ ይፋ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የፍትህ ሚንስትር፣የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፖለቲካ ፓቲዎች የጋራ ምክርቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ሲቪል ድርጅቶችና ሌሎች በርከታ ተቋማት የበላይ ሃላፊዎች ተሳትዋል፡፡

በዚህ የህዝብ ውይየት ሰለኮሚሽኑ ገለልተኛ መሆን አስፈለጊነት አስመልክተው ሃሳባቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ ( ዶ/ር ) ‹‹የብሄራዊ መግባባት ስራ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጋራ መግባባትን በየደረጃው እየፈጠረ መሄድ እንዳለበት በመጥቀስ በዚህም መደማመጥንና መተማመንን የሚያበልጽግ አሰራር ያካተተ ሆኖ መቀረጽም እንደሚገባው እናምናለን›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ የጋራ ምክርቤቱንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለያዩ አካላት አጅግ ብዙ ስራ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም አሁን በመጣው አዲስ አሰራር ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግና ብዙ ነገሮችን በመተው አካታች ያለማድረግ አይነት አካሄድ እንዳስተዋሉበት ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽነሮች አሰያየምን በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ዕጩ የኮሚሽን አባላትን ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ ይቀበላል ተብሎ የቀረበውን ድንጋጌ ከተለመደው አሰራር ወጣ በማለት በገለልተኛ አካል እንዲከናወን በረቂቅ አዋጁ ውይይቶች ላይ በተደጋጋሚ ለብልጽግና ጽህፈት ቤት እንዳቀረቡት ነገር ግን ሳይታረም እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

መንግስትም ሆነ ምርጫ ሊፈታልን ያልቻለውና በመንግስትና በህዝብ እንዲሁም በታሪከ መሃል ሲንከባለል የመጣውን ጉዳይ ለመፍታት አሁንም እየተሄደ ያለው በተለመደው አሰራር በመንግስት በኩል እንዲያልፍ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነና ይህም ገለልተኝነቱ ላይ ትልቁ ጥያቄያቸው እንደሆነ ሰብሳቢዋ ራሄል አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹እጩዎቹን ለመሰየም የፕሬዚዳት ጽህፈት ቤት እንዲይዘው ጠይቀን ነበር ነገር ግን መስተካካል አልቻለም›› ብለዋል  ራሄል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ መስከረም ገስጥ በበኩለቻው የኮሚሽነሮች አሰያየም የሌሎችን አገር ልምዶች በመረዳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጠቅላይ ሚንስተር ጽህፈት ቤት የሚለው ቀርቶ ከአስፈጻሚው አካል በጸዳ መልኩ እንዲከናውን የሚለውን ሃሳብ እንደግፋለን ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሰያየሙንም ሆነ ሂደቱን የሚመራ በህዝብ ተወካዮች ስር ያለ ወይንም ከዛ ውጭ ያለ ገለልተኛ ተቋም ወይንም ቡድን እንዲይዘው ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የፍትህ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለአሰያየሙ ከቀረቡ አማራጮች ውስጥ በተለይም ከኢትዮጵያ ገለልተኛ ከሚባሉት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ ጠቋማት አሰያይም ሂደት መተከል ለምን እንደማይቻል መልስ ሲሰጡ እነዚህ ሁለት ተቋማት ከሌሎች ተቋማት ለየት ባለ  ሁኔታ በህገ መንግሰቱ አንቀጽ 55 አማካኝነት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሚያቋቋማቸው ተቋማት በመሆናቸው ህገመንስታዊ አፈጣጠራቸው የተለየ ባህሪ ያለው በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ዕጩዎችን አንዲያቀርቡ በሚል የቀረበው ሀሳብ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ለመንግስት እጩዎችን ለይቶ እንዲሰራ ማድረጉ ከህገመንግስቱ በተጨማሪ የፕሮቶኮልና የስልጣን ጥያቄ የሚያስነሳ ሊሆን እንደሚችል ነገር ግን የህዝብ ተወካዮች ምክቤት አፈጉባኤ ተብሎ መጠየቁ አግባብነት እንዳለውና ይህ ሁኔታም ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]