Addis Ababa, Ethiopia: office buildings in the central business district – photo by M.Torres

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በትግራይ ክልል ባለፉት ወራት የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለየ ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ በክልሉ አዲሱም የቀድሞውም የገንዘብ ኖት ጥቅም ላይ እየዋለ ይቀጥል መባሉን ዋዜማ ራዲዮ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች።


አሮጌውን ብር በአዲሱ የመቀየሪያ ጊዜ ከመስከረም 6 ቀን 2013 አ.ም ጀምሮ ታህሳስ 6 ቀን 2013 አ.ም የጊዜ ገደቡ የተጠናቀቀ ቢሆንም በትግራይ ክልል ግን አሁን ድረስ አሮጌውም አዲሱም ብር ጥቅም እየዋለ መሆኑ ተነግሯል።

በክልሉ ሁለቱም የገንዘብ ኖቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው የሚያበቃበት የጊዜ ገደብ እስካሁን ያልተቀመጠ ሲሆን : በጉዳዩ ሰፊ ምክክር እየተደረገበትና ብሄራዊ ባንክ ውሳኔ እስኪያሳልፍ ሁለቱም የገንዘብ ኖቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው እንደሚቀጥልም ሰምተናል።


መንግስት የብር ለውጡን ይፋ ባደረገ በ1 ወር ከ20 ቀኑ ላይ በተቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነት በክልሉ የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠው። በዚህ ሳቢያ በትግራይ ክልል መሉ ለሙሉ የባንክ አገልግሎት እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ተቋርጦ ቆይቷል።

የብር መቀየሪያ ቀነ ገደብ ከማለቁ ከአንድ ወር በላይ እየቀረው በትግራይ ክልል የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የገንዘብ መቀየሪያው ጊዜ ታህሳስ 6 2013 አ.ም ተጠናቆም በትግራይ ክልል በርካታ መጠን ያለው አሮጌው ብር በህብረተሰቡ እጅ ላይ ቆይቷል።

አሁንም በክልሉ ያለው የመሰረተ ልማት አቅርቦት አስተማማኝነት ታይቶና ወደ ስራ የገባው የባንኮች እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ገብቶ የአሮጌው ብር የአገልግሎት ጊዜ ላይ መንግስት ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሰምተናል።


በትግራይ ክልል የህወሀት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የፌዴራል መንግስት የኣአፀፋ እርምጃ በወሰደባቸው ጊዜያት በክልሉ ያሉ የባንኮችን ሁኔታ ማወቅም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

ህወሀት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ጥቅምት 24 2013 አ. ም ምሽት ወደ ትግራይ በአሮጌው ብር እንዲቀየር ተልኮ የነበረው 1.3 ቢሊየን አዲሱ ብር መዳረሻም እስካሁን ግልጽ እንዳልሆነ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። [ዋዜማ ራዲዮ]