ዋዜማ ራዲዮ- ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ መቀዛቀዙን ተከትሎ አዳዲስ ስልቶች እየታዩ መምጣታቸውን ታዝበናል፡፡ በተለይም የመኖሪያ ቤትን በተሸከርካሪ እንቀይራለን የሚሉ የሽያጭ አማራጮችም በስፋት እየተስዋሉ መምጣታቸውን ዋዜማ ተመልክታለች ፡፡

የቤቱን መገኛ አድራሻ እና የቤቱን ይዞታ በፎቶ ግራፍ ጭምር አስደግፈው የሚወጡት እኚሁ  የፌስቡክ እና ትዊተር ማስታወቂዎች የቤቱን ዋጋ ካስቀመጡ በኃላ የመኪናውን አይነት በመግለጽ በተሸከርካሪ መቀያየር እንደሚቻል አማራጭ የሚስቀምጡ ናቸው፡፡

በዚህ መንገድ ከሚሰራጩ ማስታወቂያዎች መካከል ወደ ሁለቱ ደውለን ገዥ በመምሰል ለመደራደር ሙከራ ያደረግን ሲሆን ይህ የግብይት ተግባር በጣም እየተለመደ የመጣ ስለመሆኑ ሽያጩን ከሚፈጽሙት ሰዎች ምላሽ ለመረዳት ችለናል፡፡

በማህበራዊ  ድረ ገጽ ከሚቀመጠው የዋጋ ተመን እና የተሸከርካሪ አይነት በተጨማሪ የቤት ሻጮቹ ሌሎች ተጨማሪ አማራጮችን ያቀርባሉ፡፡ ዋዜማ ሁኔታውን ለማጣራት ብላ የደወለችለት የመኖሪያ ቤት ሻጭ ተሸከርካሪው ከተገመተው የቤቱ ዋጋ በላይ የሚተመን ከሆነ ልዩነቱን በመክፈል ቤቱን በመኪና ለመቀየር የተደራደረ ነው፡፡ ነገር ግን የተሸከርካሪውን ዋጋ የማስተመን እና የተሸከርካሪውን ቁመና የማስመርመር ግዴታን ከባለ ተሽከርካሪው የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ላለፉት 9 አመታት በቤት ማሻሻጥ ስራ ላይ የተሰማራው ምንጫችን እንደሚለው ከቀናት በፊት በገላን አካባቢ የሚገኘውን በ175 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውን እና የማጠናቀቂያ ሥራ (ፊኒሺንግ) ብቻ የቀረውን ኤል ሼፕ ቤቱን በሲኖ ተሸከርካሪ ለመቀየር የሚፈልግ ደንበኛ ወደ እርሱ እንደመጣ ይናገራል፡፡

ከዚህ ቀደም ባሳለፈው ቤት የማሻሻጥ ልምዱ እንደሱ ባሉ ሰዎች ቀድመው ይከበቡ የነበሩት ሻጮች እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን አሁን ሻጭ እንጂ የቤት ገዥ በመጥፋቱ ምክንያት እንደኛ ባሉ ሰዎች የሚከበቡት ገዥዎች ናቸው ሲል የሁኔታውን ተገላቢጦሽ ያነጻጽራል፡፡

ቤትን በመኪና የመቀያየሩ ስልት የወለደው ምናልባት አንድም ገዥ በመጥፋቱ የመጣ ከችግር የመውጫ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል የሚያነሳው ይኸው አስተያየት ሰጪ ሌላው ግን በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለው ሁኔታ ባለው የፖለቲካ ድባብ  የፈጠረው ያለመተማመን ስሜት ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡

ሌላው  መኖሪያ ቤትን እንደማስያዣ አቅርቦ ከባንኮች ብድር መጠየቅ አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ሁኔታውን ለማጣራት የጠየቅናቸው የባንክ ዘርፍ ባለሙያዎች  እንደሚሉት ግን ችግሩ ያለው ባንኮቹ ጋር ሳይሆን ደንበኞች ቤታቸውን ለማስያዝ የሚስፈልጋቸውን ህጋዊ ሰነዶች ከክፍለ ከተሞች በቀላሉ ማግኘት አለመቻላቸው ነው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ቤቶች ላይ ከጸረ ሙስናው እንቅሰቃሴ ጋር ተያይዞ የሽያጭ እግድ መውጣቱ ይህን ተከትሎ ህጋዊ ሰነዶችን አረጋግጦ መስጠት ላይ ግዜ የሚወስድ ስራ ሆኖ መምጣቱ ሰዎች እንዲህ አይነት አማራጮችን ወደ ማየት ሊገፋቸው እንደሚችል ያስረዳሉ። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/nYeVyMDNN14