Chaltu Sanni-FILE

ዋዜማ ራዲዮ-መንግስት እየተገባደደ ባለው የ2014 በጀት ዓመት በተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች 49.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 5.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መገኘቱን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስቴር ገለፀ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አንደኛ አመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባ  የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስቴርን የ2014 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ አስር ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የሚንስቴሩን ሪፖርት ለፓርላማው ያቀረቡት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የቤት አቅርቦት ጉዳይ የትም ዓለም ላይ ችግር እንዳለ ቢታወቅም የኢትዮጵያን ችግር እያወሳሰበ ያለው የድህነት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት አመታት የቤት ፋይናንስ ስትራቴጅ ትልቅ ማነቆ ሆኖ መቀጠሉንና መንግስት ባሉ የቤት ልማት ፕሮግራሞቹ እስካሁን እየተደጎሙ የነበሩት ድሆች አለመሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

በቀጣይ አመታት 80 በመቶ የሚሆነውን የቤት ልማት ፍላጎት በግሉ ዘርፍ እንዲሞላና ቀሪውን 20 በመቶ በመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት በማልማት ዝቅተኛ  ገቢ ላላቸው ዜጎች ያቀርባል ብለዋል፡፡

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስቴር በ2014 ዓ.ም በ10/90፣ 20/80፣ 40/60  በመንግስት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከ 22 ሽህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በፋይናንስ እጥረት  ምክንያት ምንም አይነት ግንባታ ማካሄድ እንዳልቻለ ሚንስትሯ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ በጀት ዓመት በመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት ከ20ሽህ ባላይ ቤቶች ለመገንባት ተይዞ የነበረው ዕቅድ የማስተግበሪያ ደንቦች ባለመፅደቃቸው ወደ ስራ አለመገባቱን፣ በኪራይ ቤት ፕሮግራም 3600 በቶችን ለማልማት ታቅዶ 2600 ቤቶች ብቻ መገንባታቸውንና እንዲሁም በሪል ስቴት ዘርፍ 12ሽህ ቤቶች ለማልማት ታቅዶ 1900 ቤቶች ብቻ መገንባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2014 በጀት ዓመት በአስር ክልሎች እና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድሮች በማህበራት የቤት ልማት  ከ 50 ሽህ የሚበልጡ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 26ሽህ ቤቶች ብቻ መገንባታቸውን እና በጆይንት ቬንቸር የቤት ልማት ዕቅድ 5600 ቤቶችን ለማልማት ታቅዶ 388 ቤቶች ብቻ እንደተገነቡ ለምክርቤቱ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም በፋይናንስ ዕጥረት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ላሉ 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና 40/60 ቁጠባ ቤቶች  አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ለባለዕድለኞች ማስተላለፍ አለመቻሉን ወ/ሮ ጫልቱ አክለው ገልፀዋል፡፡

በሁሉም ከተሞች የቤት ዕጥረት ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ሚንስትሯ ‹‹ሁሉም ሰው የቤት ባለቤት መሆን አይችልም›› ይሁን እንጅ ሁሉም ሰው የቤት ባለቤት እንኳ መሆን ባይችል አማራጭ የቤት ልማቶች አቅርቦት በተለይም ቁጥጥር የሚደረግበት የቤት ኪራይ አቅርቦት መኖር አለበት ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ቤቶችን ከተሞች ላይ መገንባት የቤት ችግርን የማይፈታና ይባሱንም ፍልሰት የሚጨምር አሰራር በመሆኑ የክልል ከተሞችና የገጠር ማዕከላት ላይ አማራጮችን እንፈጥራለን ብለዋል ሚንስትሯ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለት አመት በፊት ስራ ላይ ባዋለው የአስር አመት የልማት ዕቅድ በየአመቱ 400 ሽህ ቤቶችን ወይንም በአስር አመት 4.4 ሚሊዮን ቤቶችን በመገንባት በአስር አመት ውስጥ ቢያንስ 80 በመቶ የሚሆነውን የቤት ፍላት ችግር ለመቅረፍ በሚል የተቀመጠ ቢሆንም እስካሁን የተገነቡ ቤቶች እዚህ ገባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ 

በአስር አመት ዕቅዱ መንግስት እንዲገነቡ ይደረጋል ተብለው ለሚታሰቡት ቤቶች የፋይናንስ ምንጮችና ፖሊሲ ዝግጀት አስቀምጦ የተነሳ ቢሆንም የአስር አመት የልማት እቅዱ ትግበራ ላይ በገባ ሁለተኛ አመቱ መንግስት በእቅዱ መሰረት ላለመሄዱ የፋይናንስ እጥረት፣ የደንቦችና መመሪያዎች አለመፅደቅን ይጠቅሳል፡፡

በ1997 ዓ.ም. የተመዘገቡ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቋሚነት እየቆጠቡ የቤት ዕጣ ይወጣልናል በሚል ላለፉት 18 ዓመታት በመጠባበቅ ይገኛሉ፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]