ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ብርን ከተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች በተለይም ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ያለውን የምንዛሬ አቅምን በየእለቱ በፍጥነት እያዳከመ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።

ይህን ዘገባ ያጠናቀርንበት እለትን ጨምሮ ባሉት 16 ተከታታይ የቀደሙ ቀናት በብሄራዊ ባንክ የወጣው ንግድ ባንኮች የአሜሪካ ዶላርና ሌሎች ምንዛሬዎችን እንዲገዙና እንዲሸጡበት ያወጣላቸው ተመን ባልተለመደ ሁኔታ ጭማሬን ያሳየ ነው።

ለአብነት ህዳር 3 ቀን 2012 አ.ም የንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን ሲገዙበት የነበረው ዋጋ 29 ብር ከ4966 ሳንቲም ብር ነበር።ይህን ዘገባ በሰራንበት ህዳር 18 ቀን 2012 አ.ም ንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን የሚገዙበት ዋጋ 30 ብር ከ5181 ሳንቲም ሆኗል።በ16 ቀናት ውስጥ ንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን የሚገዙበት ዋጋ በ 1 ብር ከ 0215 ሳንቲም ጨምሯል ማለት ነው። ይህ ማለት በ16 ቀናት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር የምንዛሬ ተመን ከአሜሪካ ዶላር አንጻር በ3.4 በመቶ እንዲዳከም ወይንም( devaluation) ተሰርቷል ማለት ነው።

የአንድ ዶላር ዋጋ 2010 አ.ም ከነበረበት ሁለት ብር ለመጨመር ሁለት አመት ወስዶ ነበር። አሁን ላይ አንድ ብር ለመጨመር 16 ቀናትን ብቻ መጠየቁም አንዳች አይነት ለውጥ መኖሩን ጠቋሚ ነው።


መንግስት በጀት አመቱን ሲጀምር በቀደሙት አመታት እንዳደረገው ሁሉ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በስድስት በመቶ ብቻ እንዲቀንስ ነበር አደርጋለሁ ያለው። በ16 ቀናት ውስጥ ብር በ3.4 በመቶ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር መቀነሱ ወይንም ማዳከሙ ግን መንግስት የእቅድ ክለሳ ማድረጉን የጠቆመ ሆኗል።


በሀገሪቱ የየእለት ምንዛሬ አሰላል በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲህ አይነት የምንዛሬ ልዩነት ታይቶ አይታወቅም። ከህዳር 3 ቀን 2012 አ.ም በፊት ባሉት ቀናት ውስጥ በየእለቱ የንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን የሚገዙበት ዋጋ በአማካይ የ0.01 ሳንቲም ጭማሬ ነበር ሲያሳይ የነበረው ። ባለፈው አመት ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሀሴ አጋማሽ ባሉ ስልሳ ቀናት ደግሞ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን የሚገዙበት ዋጋ ያሳየው ጭማሬ የ23 ሳንቲም ብቻ ነው። ከህዳር 3 2012 አ.ም ወዲህ ግን በየእለቱ የንግድ ባንኮች የአንድ አሜሪካ ዶላር መግዣ ዋጋ በአማካይ የ10 ሳንቲም ጭማሬን እያሳየ ነው። በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ከ95 ቀናት በሁዋላም የንግድ ባንኮች የአንድ አሜሪካ ዶላር ዋጋ 40 ብር ይሆናል።


መንግስት የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን የሚያዳክመው ከኤክስፖርት የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ነግረውናል። እርግጥ የገንዘብ የምንዛሬ ተመንን ከሌሎች የንግድ አጋር ሀገራት መገበያያ አንጻር እንዲቀንስ ማድረግ የወጪ ንግድን እንደሚያበረታታ ኢኮኖሚስቶችም ይስማማሉ። ይህ የሚሆነውም ምርት ላኪዎች ለሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ በብር የተሻለ ዋጋን ስለሚያገኙ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ይበረታታሉ፣ የምርቶች ዋጋንም በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ያደርጋል ፣ በጥቅሉም ምርት መላክን አዋጭ ስራ ያደርገዋል በሚል እሳቤ ነው።

በእርግጥ የመንግስት ስሌት ይህ ከሆነና የብር ምንዛሬ ተመንን ማሻሻል ከፈለገ በ2003 እና በ2010 አ.ም እንዳደረገው ነገሩን ይፋ አድርጎ እንዲሁም በትንሹ ሳይሆን ለምን በጅምላ የተመን ማሻሻያ ማድረግ አልፈለገም የሚል ጥያቄ ያስነሳል።


የኢትዮጵያ መንግስት ከወጭ ንግድ የሚገኝ ገቢን ያሳድጋል ብሎ በ2003 አ.ም በ22 በመቶ በ2010 አ.ም ደግሞ በ15 በመቶ ከንግድ አጋር ሀገራት ጋር ያለውን የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማዳከሙ ይታወቃል። ሆኖም የተደረጉት የምንዛሬ ተመን ማሻሻያዎች በሁለቱም ጊዜ የሀገር ውስጥ የምርቶች የዋጋ ግሽበትን ከመጨመር ያለፈ ፋይዳ አላመጡም።

የብር የምንዛሬ ተመን መዳከም የገቢ እቃዎች መወደድን ያመጣል ፣ ምክንያቱም አስመጪዎች ለሚያመጡት ምርት ምንዛሬን ሲጠይቁ የሚከፍሉት ብር ስለሚጨምር ግሽበት ፈጣሪ መሆኑም በምጣኔ ሀብት ሙያተኞች ይታመናል። በኢትዮጵያ በ2003 አ.ም የምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ሲደረግ እስከ 40 በመቶ የደረሰ የዋጋ ግሽበት መፈጠሩ የሚታወስ ነው።

የ2010 አ.ም እርምጃም ተመሳሳይ ግሽበትን ፈጥሮ በገቢ እቃዎች የሚሰሩ በርካታ ግንባታዎች ሳይቀር በዋጋ መወደድ ምክንያት ተቋርጠዋል። አሁን ታዲያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንደበፊቱ በአንድ ከፍ ባለ መቶኛ ሳይሆን በየእለቱ የሚደረግ ጭማሬን እያደረገ ነው። ይኼን ሙያተኞቹ ፈጣን የምንዛሬ ተመን መቀነስ ወይንም ( fast depreciation ) ይሉታል። መንግስት ይህን መንገድ ተመራጭ ያደረገው በአንዴ በጅምላ በሚደረግ የተመን ማሻሻያ ምክንያት ሊፈጠር የሚችል ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከልና ገበያው ብዙም ሳይረበሽ ማስተካከያ ለማድረግ በሚል ነው ተብሏል። በዚህ ሳቢያ የሚመጣ ፖለቲካዊ ጫናን ለመቀነስም ታስቦ ሊሆን ይችላል።


አንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋው አርባ የኢትዮጵያ ብር ቢሆን ምናልባት በመግዛት አቅም ስሌት ትክክል እንደሆነ ያነሱልን አንድ ስማቸው ያልጠቀሱልን በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብት የኢትዮጵያ መገበያያ ብር አሁንም ቢሆን በጠንካራነቱ የሚገለጽ ነው ብለውናል። ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ትክክለኛ ዋጋው አንድ ዶላር አርባ ብር መሆኑንም ገልጸውልናል።

ነገር ግን የምንዛሬ ተመኑ መዳከሙ መንግስት እንደሚለው የወጪ ንግድን ከማበረታታት ይልቅ የዋጋ ግሽበት የመፍጠር እድል ነው ያለው። ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ የምንዛሬ ተመን ማሻሻያዎችም ሆኑ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታም ለዚህ ምስክር ነው። የሩቅ ምስራቅ ሀገራት የምንዛሬ ተመናቸውን ሲያዳክሙ ካጋጠማቸው የዋጋ ግሽበት ይልቅ የወጭ ንግዳቸው የተሻለ እድገትን አስመዝግቦላቸዋል። ሀገራቱ ምንዛሬ ከማስተካከላቸው በፊት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ምርት ብዛትና ጥራትና ተወዳዳሪነት ላይ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ስራቸውን አጠናቀው ነው። በዚህ ጊዜ የምንዛሬ ተመንን ማምጣት በወጪ ንግድ ላይ ውጤትን ያመጣል።


በኢትዮጵያ ለሁለት ጊዜ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሲዳከም ግን የኤክስፖርት ዘርፉ ያለበት ችግር ሳይቀረፍ የተለመዱ የግብርና ምርቶችን ለመላክ ተብሎ ነው። በሁለቱም ጊዜ ለውጥ አልመጣም። ሊያውም በ2010 አ.ም የምንዛሬ ተመን ሲዳከም ሀገሪቱ አይደለም ለወጪ ንግድ ብቁ ዝግጅት ልታደርግ ከአንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥታ ወደ ሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ልትገባ የምትንደረደርበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነበረች።

የብሄራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ፍጹም አሰፋ ባለፈው አመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በ2010 አ.ም የተደረገው ብርን የማዳከም ውሳኔ የታሰበውን ለውጥ አላመጣም ብለዋል። የወቅቱ ውሳኔም የእነ አለም ባንክና አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ጫና እንዳለበት ይነገር ነበር። ይህ እየታወቀ አሁን መልኩን የቀየረ የተመን ማሻሻያ መደረጉ የተለየ ውጤት ማምጣት መቻሉ ላይ ጥያቄን ያስነሳል።

ለወጪ ንግዱ ስኬማነትም ቢሆን ሀገሪቱ ያለችበት የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ነው ማለት አይቻልም። ኢትዮጵያ አሁንም ኢኮኖሚዋ የተመሰረተው በዋናነት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች በመሆኑ ነው።ነዳጅን መንግስት እየደጎመ ቢቀጥል እንኳ የግንባታን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች ከውጭ ሲገቡ መወዳዳቸው አይቀርም ።አሁን ላይ ያለው የዋጋ ግሽበትም ለሀገሪቱ ፈታኝ ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]