FILE

ዋዜማ ራዲዮ-የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን፣ የግብርና የፀረ ተባይ እና ፀረ አረም መድሃኒቶችን በማምረት የሚታወቀው አለማቀፉ ኮርቴቫ አግሪሳይንስ ኩባንያ በ2013 ዓ.ም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እርሻ ላይ መሰብሰብ የነበረበትን ምርጥ ዘር በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ምርት ሳይሰበስብ መቅረቱን ዋዜማ ከኩባንያው ሰምታለች፡፡

የኩባያው የኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ይልማ ለዋዜማ እንደገለጹት በጸጥታ ችግር ምክንያት በቤንሻንጉል ክልል ብቻ መሰብሰብ የነበበረበት በ700 ሄክታር መሬት ላይ ተዘርቶ የነበረ ምርጥ ዘር አለመሰብሰቡን፣ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ አለልቱ መሰብሰብ የነበረበት ምርጥ ዘር አለመሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ይህ የግብርና ስራ ግብዓት አቅራቢ ኩባንያ ለ2013 ዓ.ም የእርሻ ወቅት ከ150ሽህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ሰብስቦ እንደነበር የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ በ2014 ከኩባያው ለክልሎች እያቀረበ ያለው አጠቃ ላይ የምርጥ ዘር ምርት ከ60ሽህ ኩንታል እንደማይበልጥ አመላክተዋል፡፡

ኩባንያው የግብርና ግብዓቶችን በ2013 በሶስት ክልሎች ለመሰብሰብ አቅዶ፣ መሰብሰብ የተቻለው ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ብቻ እንደሆነ አቶ ፋሲል  አክለው ገልጸዋል፡፡

ኩባያው በየአመቱ ከ3000 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ምርጥ ዘር ያመርት እንደነበር የገለጹት አቶ ፋሲል በ2013 ዓ..ም ግን 2000 ሄክታር መሬት መድረስ ከባድ እንደሆነበት አመላክተዋል፡፡

‹‹ፍላጎቱ እየጨረ በመምጣቱ ምክንያት ምርጥ ዘር የማይፈለግ የለም፤›› ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ በጸጥታ ችግርና በውጭ ምንዛሬ እጦት ምክንያት የታሰበውን ማሳካት አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዳሉ።።

ብዙውን ጊዜ የበቆሎ ምርጥ ዘር በማምረት የሚታወቀው ይህ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከበቆሎ ብቻ ከሚፈለገው ምርጥ ዘር እስከ 45 በመቶ የሚሸፍን ኩባንያ ነው፡፡፡ 

በጸጥታ ችግር ምክንያት የኩባንያው ባለሙያዎች ማሳውን በቅርብ ሄደው ሊንከባከቡ ባላመቻላቸው ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ስርቆትና ውንብድና እንደገጠማቸውም ሀላፊው ተናግረዋል።

በዚህ የምርጥ ዘር አቅርቦት ዕጥረት ምክንያት በተያዘው የመኸር ዘመን ለገበሬው በቂ የሆነ ምርጥ ዘር ማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን አቶ ፋሲል ገልጸዋል፡፡ ዋዜማ ራዲዮ