Lideta Higher Court
Lideta Higher Court

ዋዜማ ራዲዮ- ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የፍርድ ቤቶች ዳኞች በጥልቀት ለመታደስ በየችሎቱ መሽገዋል፡፡ ችሎት የሚያስችሉባቸው አዳራሾች ዉስጥ በስብሰባ ተሰንገው ጠዋት ገብተው ማታ እየወጡ ይገኛሉ፡፡ የልደታ የመጀመርያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሺህ የሚቆጠሩ ተመላላሾችን በየቀኑ ያስተናግዳል፡፡ ባለጉዳዮች ባለፉት ቀናት ከፍ ያለ እንግልት የደረሰባቸው ሲኾን ይህን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተገልጋይ ለመቀነስ በዳኞች ቢሮዎች ላይ ሁሉም ቀጠሮዎች ከመጋቢት 13 ወዲያ እንደተሸጋገሩ የሚገልጽ ደብዳቤ መለጠፍ አስፈልጓል፡፡

“የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች በዘፈቀደ አይሰጡም፡፡ እነሱ በሚሉት ቀን ሌላ ችሎት ሊኖርብን ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የፍትህ ሥርዓቱ ላይ እየቀለዱ ነው ያሉት” ይላሉ ለዋዜማ ሐሳባቸውን የገለጹ በማንኛውም ፍርድ ቤት ጠበቃ ኾነው የሚሠሩ ግለሰብ፡፡

በዚህ የጥልቅ ተሀድሶ መርሐግብር ከ5ሺህ ብር በታች የኾኑ ጉዳዮች ከሚታዩባቸው የቀበሌ የማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ዉጭ ያሉ ሁሉም ፍርድ ቤቶች ዝግ ኾነዋል፡፡ ስድስት ኪሎ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ እንዲሁም ሰበር ሰሚ ችሎት፣ ሁሉም የመጀመርያ ፍርድ ቤቶች፣ ሁሉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በየምድባቸው ተሀድሶ ገብተዋል፡፡ በጥልቅ ተሀድሶው የኢህአዴግ ፓርቲ አባል የኾኑ ዳኞች ብቻ ሳይሆኑ ቁጥራቸው ጥቂት ቢኾንም ሌሎች የፓርቲ አባል ያልኾኑ ገለልተኛ ዳኞችም የመሳተፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

በድምሩ 14 የሚኾኑ ዳኞች የሚገኙትበት የሁለቱ የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ በቁጥር 30 የሚኾኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና ረዳቶቻቸው፣ ልደታ ፍርድ ቤት የሚገኙ 16 ችሎቶችን ጨምሮ፣ የካ፣ አራዳ፣ ቦሌ፣ ቄራ፣ ጎፋ፣ ሰባራ ባቡር፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሁሉም ሥራ ዘግተው ለጥልቅ ተሀድሶ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተሰምቷል፡፡

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በርካታ ፋይሎችን የሚያስተናግደውና 6 ኪሎ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ፊትለፊት የሚገኘው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፍ/ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ሁሉም ሠራተኞቹ ለጥልቅ ተሀድሶ በመፈለጋቸው ለሚቀጥሉት 15 ቀናት ሙሉ በሙሉ ዝግ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡ ይህ ቢሮ በርካታ ባለጉዳዮችን በየቀኑ የሚያስተናግድ ከመሆኑ አንጻር ለዚህን ያህል ጊዜ መዘጋቱ ከፍ ያለ ሕዝብ እሮሮ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ምናልባት የባለጉዳዮች ቅሬታ ከበዛ ተሀድሶው ወደ አንድ ሳምንት ዝቅ ሊደረግ እንደሚችል ይገመታል፡፡

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በክፍለ ከተሞች አካባቢ በነበረ የጥልቅ ተሀድሶ የተራዘመ መርሀግብር ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች መንገላታታቸውን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢው ኅብረተሰብ እሮሮው እየጨመረ በመምጣቱ ከጥበቃ ኃይሎች ጋር መጠነኛ ግብግብ በመፈጠሩ ስብሰባዎች ወደ ምሽት እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ብቻ እንዲካሄዱ በክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ተወስኖ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቶች ከክፍለ ከተሞች ያልተናነሰ በርካታ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግዱ ተቋማት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

በመጀመርያ፣ በከፍተኛና በጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በ12 ወራት ጊዜ ዉስጥ ብቻ ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ መዝገቦች ይከፈታሉ፡፡ ከዓመት በፊት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የቀረበ አንድ ሪፖርት እንደሚያትተው በ2006 ዓ.ም  ብቻ 91ሺህ 594 አዳዲስ ፋይሎች ሲከፈቱ ከዚህ ዉስጥ 46 ከመቶው ፍትሐብሔር፣ 36 ከመቶው ወንጀል፣ 9 ከመቶው ለሰበር የቀረቡ ናቸው፡፡ በዓመቱ ከቀረቡት 96ሺህ አዳዲስ መዝገቦች 11ሺህ የሚኾኑት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ 15ሺህ የሚኾኑት ለከፍተና ፍርድ ቤት እንዲሁም 64ሺህ የሚኾኑት ለመጀመርያ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ የፍትህር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ዉሳኔ ሳያገኙ ወደ አዲስ ዓመት የሚተላለፉ ፋይሎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ከ2006 ወደ 2007 ዓ.ም ዉሳኔ ሳያገኙ የተላለፉ ፋይሎች ቁጥር 34ሺህ ይጠጋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመዝገቦች መጨናነቅ (congestion rate) በሁሉም ፍርድ ቤቶች አካባቢ እጅግ የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ ሪፖርት የቀረበ አንድ ሰነድ እንደሚያትተው አንድ የፍዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ በአማካይ በዓመት 530 ፋይሎችን እንዲመለከት ይገደዳል፡፡ ይህ መረጃ በ2006 ዓ.ም 160 ዳኞች ባሉበት ወቅት የተሰበሰበ አሐዝ ቢኾንም የዳኞች ቁጥር በእጥፍ ባደገበት በአሁኑ ወቅትም ቢኾን ኹኔታዎች እምብዛም እንዳልተሻሻሉ ይነገራል፡፡

ለዚህም የዳኞች በሥራቸው ደስተኛ ያለመኾንና ፋይሎችን በጊዜ ለማየት ዳተኝነት መኖር፣ የመንግሥት በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እጁ መርዘም በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ሳይፈረድባቸው በእስር ላይ ያሉና በርካታ ዓመታትን በቀጠሮ ማረሚያ ቤቶች የቆዩ በርካታ ዜጎች እንዲኖሩ አስችሏል፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዉስጥ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ጨምሮ ወደ 2ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መሐል ሦስት መቶ የሚጠጉት ዳኞች ናቸው፡፡