ዋዜማ ራዲዮ- በከፍተኛ ደረጃ የተበላሸ ብድር ቀውስ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካለበት ችግር እንዲወጣ ያስችለዋል የተባለ ጥናት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በብሄራዊ ባንክ ትእዛዝ እየተካሄደ ነው። ጥናቱ የሚራውም በቅርቡ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ በተሾሙት ተገኝወርቅ ጌቱ መሆኑን ሰምተናል።


በልማት ባንኩ ላይ የሚሰራው ጥናት ከ2008 እስከ 2009 አ.ም ከተደረገው በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ያተኮረ የብድር ቀውስ ፍተሻ ይሰፋል። የአሁኑ ጥናት ልማት ባንኩ በጥቅሉ ብድር ያቀረበላቸው ዘርፎችን ያጠቃልላል።


ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም እንደዘገበችው ልማት ባንኩ ከሰጠው ከ39 ቢሊየን ብር በላይ ብድር 51.6 በመቶው ወይንም 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋው ብድር የተበላሸ ብድር ሆኗል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የባንኩ የተበላሸ ብድር ከተጠቀሰው በላይ እየተባባሰ እንደመጣ መረጃዎች አሉ። ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ በተለይም የቱርክ ኩባንያዎች እንዲሁም ጋምቤላ ውስጥ ሰፋፊ እርሻ ላይ እንሰማራለን ላሉ ግለሰቦች ፣ (እዚህ ውስጥ የህንድ ኩባንያዎችም ይገኛሉ) ፣ በተበላሸው ብድር ምጣኔ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
የባንክ የስራ ሀላፊዎች እንደሚናገሩት ከሰፋፊ የእርሻ መሬት ጋር ተያይዞ የተሰጠው ብድር የተፃፈ ህግን ባይጥስም ብድሩ እንዳይመለስ ሆነ ተብሎ በጥቅም ትስስር የተካሄደ ነው። በዚህም 6.3 ቢሊየን ብር ብድር ተሰጥቷል። ገንዘቡን ለማስመለስ በህግ አግባብ ለመሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ከባንክ ባለስልጣናት መግለጫ ተረድተናል።


በቅርቡ ከግኝቱ እስከ ምክረ ሀሳቡ ለመንግስት የሚቀርበው ጥናት ከአደረጃጀትና መሰል እርምጃዎች ጨምሮ የልማት ባንኩን የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስነዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቻችን ሰምተናል።


ባንኩ በምንም ደረጃ የችግሩ ምንጭ ቢለይ ግን ባከነ የተባለውን ገንዘብ የማስመለሱ እድል ጠባብ እንደሚሆንከዘርፉ ባለሙያዎች አስተያይት ተረድተናል። ምክንያቱም የባንኩ ገንዘብ ለብድር የወጣው ቋሚ ላልሆኑ ንብረቶችም በመሆኑ ነው። ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻ አልሚዎች ከተሰጠው 6.3 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ብዙውን ለስራ ማስኬጃ የተሰጠ ነው ።

በሌላ በኩል ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ብድር የወሰዱ ኩባንያዎችም ጉዳይ እንዴት እንደሚፈታ አሳሳቢ ሆኗል። እንደ ኤልሲ አዲስ አይነት ኩባንያዎች ቢሊየን ብድር ይዘው ሲጠፉ ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ ተደጋጋሚ ጨረታ ቢወጣም የፋብሪካዎቹ ዋጋ እና የወሰዱት ብድር አልመጣጠን ብሎ በተደጋጋሚ ሳይሳካ ቀርቷል። የዚህ አይነት ኩባንያዎች ጉዳይም በኪሳራ ሊያልቅ እንደሚችል ይገመታል። አይካ አዲስና ኢቱር የመሰሉ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው እስከ ሁለት ቢሊየን ብር ተበድረው ብድራቸው ችግር ውስጥ መግባቱ የሚታወቅ ነው።


 በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ልማት ባንኩ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው። ለባንኩ ያልተመለሰ ብድር በብሄራዊ ባንክ የተቀመጠውን የ15 በመቶ ገደብም በእጅጉ ርቆ 50 በመቶም አልፏል።ተደጋጋሚ የአመራር ለውጥም ባንኩን ጤናማ ሳያደርገው ቆይቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]