ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመደገፍ በተደረገው ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ ተከትሎ ለጠፋው የ2 ሰዎች ህይወት እና በ150 ሰዎች ላይ ለደረሰው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ተጠያቂ ናቸው ያላቸው 5 ግለሰቦች ላይ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና በሽብር ወንጀል አዋጁ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡

በድርጊቱ ላይ እጃችው አለበት የተባሉት ተከሳሾች ጌቱ ግርማ፣ ብርሀኑ ጁፋር ፣ ጥላሁን ጌታቸው ፣ ባህሩ ቶላ እና ደሳለኝ ተስፋዬ ክርክራቸውን በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገመንግስት ጉዳዮች ችሎት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ሲመረምር የቆየው ችሎቱ ዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ረፋድ ላይ ተሰይሞ ነበር፡፡

በዚህም ድርጊቱ የተፈፀመው የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመግደል መሆኑ እና በወቅቱ ተገድለው ቢሆን ኖሮ በሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ የሰላም መደፍረስ እንደ ቅጣት ማክበጃ እንዲወሰድለት አቃቤ ህግ ያቀረበውን ጥያቄ ችሎቱ ከግምት ውስጥ አስገብቷል፡፡

በሌላ ጎን ተከሳሾችም የየራሳቸውን የቅጣት ማቅለያ ለችሎቱ አስገብተዋል፡፡፡

በዚህም መሰረት ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የለብንም እንዲሁም የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነን በማለት የቅጣት ማቅለያ ያስገቡት ጌቱ ግርማ እና ብርሀኑ ጁፋር በ23 አመት እና በ22 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ችሎቱ ወስኗል፡፡

በእለቱ ቦምብ በመወርወር ለ2 ሰዎች ህይወት ማለፍ እና 150 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ የወንጀል ድርጊቱን በቀጥታ ፈፅሟል የተባለው ጥላሁን ጌታቸው ደግሞ ምንም አይነት የቅጣት ማቅለያ ያላቀረበ ሲሆን ችሎቱም የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወስኖበታል፡፡

በእለቱ ሁለተኛውን ቦምብ ቢወረውርም ምንም ጉዳት አላደረሰም የተባለው ባህሩ ቶላ ደግሞ በ17 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ችሎቱ ወስኗ፡፡

በመጨረሻም ስለታቀደው የሽብር አላማ እና ወንጀል መረጃው እያለው ለፖሊስ ባለማሳወቅ የወንጀሉ ተባባሪ ሆኗል የተባለው 5ኛ ተከሳሽ ደሳለኝ ተስፋዬ ደግሞ በ5 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡

ታራሚዎቹ የችሎቱ የቅጣት ውሳኔ ከተሰማ በኋላ በጭብጨባ የተቀበሉ ቢሆንም የፍርድ አሰጣጡን ግን አግባብ አይደለም ሌብነት ነው በማለት ተቃውሞ እያሰሙ ከችሎት ወጥተዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]