በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ጥበቃ ስለሚደርላቸው 29 ምስክሮች ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ ከአዋጁ ውጭ በመሆኑ ማስፈፀም እንደማይችል አቃቤ ህግ ገለፀ፡፡

ዋዜማ ራዲዮ- የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ እና ሌሎች 25 የደህንነት አባላት በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል መዝገብ አቃቤ ህግ ይሰሙልኝ ያላቸውን 131 ምስክሮች ስም ዝርዝር ከክስ ቻርጅ አና የማስረጃ ዝርዝር ጋር አያይዞ አቅርቦ ነበር፡፡

ከእነዚህ ውጪ ደግሞ 29 ምስክሮችን ስለወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ በወጣው አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4 (1) (ሸ) እና (በ) መሰረት የምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓም ማመልከቻ  አስገብቶ ነበር፡፡

የአዋጁ አንቀፅ 4 (1) በተለይ (ሸ) እና (በ) ደግሞ “የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለፀ” እና “ምስክርነት በዓካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይንም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ” በማለት በቅደም ተከተላቸው ይደነግጋሉ፡፡

ሆኖም ይህንን መዝገብ እየተከታተለ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበለት ማመልከቻ ለምስክሮቹ ለምን ጥበቃ እናዳስፈለገም ሆነ የምስክሮቹ ማንነት እነማን እንደሆኑ እንደማይገልፅ በማብራራት በአዋጁ አንቀፅ 6 (2) መሰረት አቃቤ ህግ ማመልከቻውን አሻሽሎ ለችሎቱ እንዲያቀርብ እና ጥበቃ እንዲደርጋለቸው የሚፈልጉትን ምስክሮች ስም ዝርዝር ደግሞ ከመዝገቡ ጋር ሳይያያዝ ለዳኞች ብቻ እንዲያቀርቡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የአዋጁ አንቀፅ 6 (2) ምንይላል? 

ለጥበቃ ተጠቃሚነት የሚቀርብ ማመከልከቻ 

ሀ/ ጥበቃ የሚደረግለትን ሰው ማንነት እና አድራሻ የሚገልፁ መረጃዎችን

ለ/ ለጥበቃው ምክኒያት ከሆነው ጥቆማ ምስክርነት ወይም ምርመራ ጋር የተያያዘውን የወንጀል ድርጊት 

ሐ/ጥበቃ በሚደረግለት ሰው ላይ የተጋረጠው አደጋ… እያለ እስከ ሠ ድረስ የመሚዘልቅ ነው፡፡

እናም ዛሬ ችሎቱ የአቃቤ ህግን የተሻሻለ ማመልከቻ ለመመልከት ቢሰየምም አቃቤ ህግ ግን እንዳሻሽል በተጠየኩበት የአዋጁ አንቀፅ  ማለትም አንቀፅ 6 (2) መሰረት ዝርዝር ማመልከቻም ሆነ ጥበቃ የሚደረግለት ምስክር ሰም የሚሰጠው በቀድሞው አጠራር ለፍትህ ሚኒስትሩ በአሁኑ ደግሞ ለጠቅላይ አቃቤ ህጉ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

አክሎም አዋጁ ጥበቃ የሚያስፈልግቻውን ምስክሮች ማንነት እና ሌላው ዝርዝር የማመልከቻው ክፍል ለዳኛ ወይም ለፍርድ ቤት ይቅረብ ባላለበት እና የህግ አግባብ በሌለበት ማቅረብ ስለማልችል የችሎቱን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ተቸግሬያለው ሲል በፅሁፍ አቤቱታ እና በቃል ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

አዋጁ ምን ይላል?

በተጠቀሰው አንቀፅ 6 (2) በተለይ (ሠ) ላይ ከላይ ከሀ- ሠ በማመልከቻው መካተት ያለባቸውን ከዘረዘረ በኋላ በአነንቀፅ 7 (2) ስር  ሚኒስትሩ ለጥበቃ ተጠቃሚነት በቀረበ ማመልከቻ ላይ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 3 ድንጋጌዎች መሰረት በ- ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት ይላል፡፡

በዚሁ አዋጅ ስለፍትህ አካላት ሀላፊነት ሲደነግግ ደግሞ በአንቀፅ 23(1) ስር ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 1  ከፊደል ተራ (ሰ) እስከ(ተ) የተደነገጉትን የጥበቃ እርምጃዎች እንደአግባቡ መወሰዳቸውን የማረጋገጥ ሀላፊነት ይኖርበታል በማለት ፍርድ ቤቱ የጥበቃ እርምጃዎቹ ስለመፈፀማቸው የማረጋገጥ ሀላፊነት እንደተሰጣቸው ይጠቁማል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ችሎቱ የአቃቤ ህግን ምላሽ ካዳመጠ እና ከመከረ በኋላ ጥበቃ የሚደርጋለቸው ምስክሮችን ስም ዝርዝር ከመዝገቡ ጋር የሚያዝ ሳይሆን ለዳኞች ብቻ ስጡ ብለን ግልፅ ትዕዛዝ ተሰጥቶ እያለ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ማመልከቻው ተስተካክሎ ካልቀረበ በስተቀር ይህ ችሎት ጥበቃ እንዲደረግለት የሚያዘው ምንም ምስክር የለም በማለት ትዕዛዝ ሰትቷል፡፡

ችሎቱ ከዚህ ቀደም 131ን ምስክሮች ለመስማት በያዘው ቀጠሮ እንደሚቀጥል ያሳወቀ ሲሆን 29ኙን ምስክሮች በሚመለከት ግን እስካሁን ጥበቃ እንዲደረግ በችሎቱ እንዳልታዘዘ ነገር ግን አቃቤ ህግ ወደፊት ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ ተገልፅዋል፡፡