ዋዜማ – በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳና  በጋምቤላ ወረዳ  ግጭት ተቀስቅሶ ጉዳት መድረሱን ዋዜማ ከሰባሰበችው መረጃ መረዳት ችላለች። 

በኢታንግ ልዩ ወረዳ ከማክሰኞ ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት የቡድን ታጣቂዎች ጭምር የተሳተፉበት እንደነበር ከዐይን እማኞች ስምተናል። ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የጋምቤላ ክልል የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል። 

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ስር በምትገኘው ኢታንግ ልዩ ወረዳ “አካዶ” በተባለ አካባቢና በጋምቤላ ወረዳ “አቦል” በተባለ ከተማ ማክሰኞ’ለት ግጭቶች እንደተፈጠሩ ዋዜማ ከረድኤት ድርጅቶች ምንጮች ተረድታለች። በግጭቶቹ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ምንጮቹ ለጊዜው አልጠቀሱም። የክልሉ መንግሥትም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በተጠቀሱት ወረዳዎች ተፈጠረ ስለተባለው አዲስ ግጭት ያለው ነገር የለም።

የክልሉ ፖሊስ የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ለማረጋጋት ሙከራ ቢያደርግም ረቡዕ ዕለት ግጭት ተባብሶ መቀጠሉንና በአንዳንድ አካባቢዎች እሩምታ ተኩስ እንደሚሰማከ ከነዋሪዎች ሰምተናል። 

በግጭቱ የተሳተፉት ወገኖች ማን እንደሆኑ ግን የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንዲያደርግለት የክልሉ መንግስት መጠየቁንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ መከላከያ ግጭቱ  ወደተከሰተበት ቦታ አለመድረሱን ተረድተናል። 

በሌላ በኩል የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ከትናንት ምሽት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና ክልል-ዓቀፍ የሰዓት እላፊ ገደብ ማጣሉን ትናንት ምሽት አስታውቋል። የሰዓት እላፊ ገደቡ፣ ከምሽቱ 1:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ የሰዎችንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚከለክል እንደኾነ የክልሉ መንግሥት  ገልጧል።

የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ግን ከገደቡ ውጭ ባለው ጊዜ መደበኛ ሥራቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል። ሰዓት እላፊ ገደቡን መጣል ያስፈለገው፣ “በክልሉ ሰሞኑን በተከሰተው የጸጥታ ችግር” ሳቢያ እንደኾነ ገልጧል። በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ውስጥ እጃቸው አመራሮችና ሌሎች አካሌት ግድያቸው ተጣርቶ ጠያቂ እንደሚኾኑ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላና ኢታንግ ከተማ ባለፈው ግንቦት አጋማሽ በተቀሰቀሰ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች እንደተገደሉና ከ17 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። [ዋዜማ]