ዋዜማ ራዲዮ- በድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ዙሪያ ዘለግ ያለ ጊዜ የወሰደው የላምሮት ከማልና የአቃቤ ሕግ የችሎት ክርክር አሁን ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሶ በተከሳሿ ላምሮት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ስጥቷል። ተከሳሿ በግድያው ዙሪያ የቀረበባት ክስም በሂደት ተሻሽሏል።

ሐሙስ ታሕሳስ 14 ቀን 2014 ዓ. ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ተኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስት ጉዳዩች ችሎት ላምሮት ከማል በተከሰሰችበት አንቀፅ 575/1  ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠ ሲሆን ችሎቱ ከተከሳሽ ላምሮት የቅጣት ማቅለያዋን በፅሁፍ የተቀበለ ቢሆንም አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃውን በፅሁፍ ባለማቅረቡ ለዛሬ ከሰአት በቢሮ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል።

የቅጣት ውሳኔ እስኪተላለፍ (ምናልባትም ነገ) ተከሳሽ ላምሮት በአዲስአበባ ፖሊስ በእስር እንድትቆይ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ላምሮት ከማል አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሲገደል ቦታ አምቻችታለች በሚል በሽብር ወንጀል 113/2 መስከረም 2 2013 ዓም ከ 3 ተጠርጣሪዎች ጋር ክስ ተመስርቶባት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ተኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስት ጉዳዩች ችሎት ስትከታተል የቆየች ሲሆን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቂ ማስረጃ ተከሳሿ ላይ ስላላገኘሁ በነፃ ትሰናበት ሲል የካቲት 18 2013 ዉሳኔ መስጠቱ የሚታውቅ ነው

 ከሳሽ አቃቤ ህግ የተከሳሽን ነፃ መልቀቅ በመቃወም ነፃ በተባለችበት ቀን የካቲት 18 2013 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሎ በእስር እንድትቆይ አድርጓል

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርጉ የቆዩት ከሳሽ አቃቤ ህግ እና ተከሳሽ ላምሮት ከማል ጥቅምት 10 2014 ዓም የተከሰሰችበት ሽብር ወንጀል 113/2  ተቀይሮ በወንጀል ህግ 575/1 እና 2 አደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን ባለ መርዳት ወንጀል እንድትከላከል ውሳኔ ሰቶ መዝገቡን ወደ  ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ተኛ የፀረ ሽብርን ህገ መንግስት ጉዳዩች ችሎት መመለሱ ይታወቃል።

በትእዛዙ መስረት ህዳር 9 2014 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ተኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስት ጉዳዩች ችሎት ከጠበቃዋ ጋር ቀርባ ባደረገችው ክርክር የተከሰሰችበት የወንጀል ክስ አንቀፅ 575 የዋስትና ጥያቄን  የማያስከለክል በመሆኑ በ5000 ብር ዋስትና ወጥታ የመከላከያ ምስክሮቿን በህዳር 23-24 2014 ዓም እንድታሰማ የተውሰነ ቢሆንም ህዳር 23 ከእስር ተፈታ ችሎት የቀረበችው ላምሮት የመከላከያ ምስክር የለኝም በአቃቤ ህግ ማስረጃ ይፈረድብኝ  ብላ ችሎቱን ጠይቃለች።

አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22 2012 ዓም ከምሽቱ 3 ሰአት ገደማ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሉ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]