Woldiya- Photo Wikipedia
Woldiya- Photo Wikipedia

ዋዜማ ራዲዮ- የጥምቀትን በዓል አስታኮ በወልዲያ ከተማ የተቀሰቀሰው ፀረ አገዛዝ ተቃውሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወጣቶች እና ሁለት የፀጥታ ሀይል አባላት እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል፣ ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት አካላት እንደነገሩን ላለፉት ሁለት ወራት በነዋሪዎችና በፀጥታ ሀይሎች መካከል በዓይነ ቁራኛ መተያየት የነበረ ሲሆን የጥምቀት በዓል ዋዜማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ስራዊት መሳሪያ የደገኑ ተሽከርካሪዎችን ይዞ ወደ መንደሮች መዝለቁን ተመልክተዋል።
የመከላከያ ስራዊት አባላቱ ወጣቶች ላይ አፈ-ሙዝ በመደገን ስነ ልቦናዊ ፍርሀት ለመፍጠረ ሲያደርጉት የነበረው ሙከራ ሳይሳካ ወጣቶቹ ፀረ-አገዛዝ መፈክሮችናን ዘፈኖችን እያሰሙ ወደ ከተራ በዓል አመሩ።
የከተራ በዓል ዕለት ኮከብ የሌለው ባንድራ የያዙትንና መፈክር የሚያሰሙ ወጣቶችን ለመነጠል የፀጥታ ሀይሎቹ ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም።
በዕለተ ጥምቀት ለጥበቃ ከተሰማሩት የፀጥታ ሰራተኞች በአንዱ ላይ በተወረወረ መጠኑ ከፍ ያለ ድንጋይ ተመትቶ ይዘረራል።
ጥር 12 ቀን ቁጥሩ ከፍ ያለ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የክልሉ ፖሊስ የተሰማራ ሲሆን ታቦት የማስገባቱ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ በተጀመረ የድንጋይ ውርወራ በተቀሰቀሰ ግጭት ከስድስት እስከ አስር የሚደርሱ ወጣቶች ተገድለዋል ብለው እንደሚያምኑ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ሁለት የፀጥታ ሰራተኞችም ተገድለዋል።
እሁድ የሟቾችን ቀብር ለማካሄድ የተሰበሰበው ነዋሪ ከስርዓቱ ጋር ቅርበት አላቸው ባላቸው የንግድ ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ እሳት በመለኮስ እንዳቃጠላቸው ታውቋል።  ጥቃት ከደረሰባቸው ንብረቶች መካከል የከተማው ሹማምንት መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል።

በከተማው አሁንም አልፎ አልፎ ተኩስ የሚሰማ ሲሆን በፀጥታ ሀይሎች እንታፈሳለን የሚል ስጋት የገባቸው ወጣቶች ከተማዋን ትተው እየተሸሸጉ መሆኑንም ስምተናል።
ተጨማሪ መረጃ ስናገኝ እናክልበታለን።