Photo credit Wolkite city Administration

ዋዜማ- በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በመሳሪያ ማከማቻ መጋዘን ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የጦር መሳሪያ መወሰዱን የከተማው ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ለዋዜማ ገልጿል። 

ዝረፊያው የተፈጸመው ሰኞ ግንቦት 5/2016 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰአት አካባቢ እንደሆነ እና የዘራፊዎቹ ማንነት እስካሁን እንዳልታወቀም ጽ/ቤቱ አስረድቷል። 

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ትዕግሥቱ ፉጄ ለዋዜማ እንደገለጹት፣ የተዘረፈው መሳሪያ እና ሌሎችም የተቋሙ መገልገያዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለማወቅ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራ እየተሰራ ነው ሲሉ አብራርተዋል። 

ከተዘረፉት የጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ አንድ የፖሊስ ፓትሮል መኪናም እንደሚገኝበትና ዘራፊዎቹ “ቱሉ ላሜ” በሚባል የገጠር መንደር ውስጥ ጥለውት ሄደው መገኘቱን ነግረውናል። መኪናው ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ወደ ጣቢያ ተመልሶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በዘረፋው ቁጥራቸው በርከት ያሉ ጠመንጃዎች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መወሰዳቸውን ለዋዜማ ያስረዱት ትዕግሥቱ፣ ድርጊቱን የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል። 

በእለቱ የነበሩ ተረኛ ጥበቃ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝና ወንጀሉን የፈጸሙ አካላትን አድኖ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ አካላት ስለመያዛቸው አልተገለፀም።

ዋዜማም በዚሁ ጉዳይ ላይ አንዳንድ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎችን ያነጋገረች ሲሆን፣ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ ተዘረፈ ከተባለ በኋላ “ማንነት ተኮር” የቤት ለቤት ፍተሻ እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል። 

የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ለዋዜማ እንደገለጹት፣ ፍተሻው በተለይም በከተማዋ ልዩ ስሙ   ”ጉብሬ መውጫ”  በተባለ ስፍራ በሰፊው እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ፍተሻው “ማንነት ተኮር” ነው ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የመሳሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ጭምር መሳሪያቸውን ተነጥቀው ወደ እስር ቤት መግባታቸውን ተናግረዋል። 

[ስም የተዘለለ] የተባሉ የከተማው ነዋሪ ባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው እንደታሰሩባቸው ገልፀው፣ ባለቤታቸው ከሁለት ቀን እስር በኋላ ሲለቀቁ ልጆቻቸው ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

 በከተማው ከአርባ ዓመታት በላይ መኖራቸውን የሚናገሩ  ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው የንግድ ድርጅታቸውን ለመጠበቅ ከሀያ አምስት ዓመታት በፊት ፈቃድ አውጥተው የታጠቁትን መሳሪያ በዞኑ የፀጥታ ሰራተኞች መነጠቃቸውን ነግረውናል። 

ዋዜማም የነዋሪዎቹን ሃሳብ ይዛ የከተማውን ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቀች ሲሆን፤ እሳቸውም፣ በከተማዋ አንድም ከብሔሩና ማንነቱ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረገ አካል የለም ሲሉ አስተባብለዋል። 

የወልቂጤ ከተማ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ከተሞች በተለየ ከሁሉም ብሔር የተወጣጡ የአገሪቱ ዜጎች ተቻችለው የሚኖሩባት ናት የሚሉት ትዕግሥቱ፣ ፖሊስ የሚጠረጥረው አካል ካለ ግን በብሔር ማንነት ሳይለይ ሁሉም ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር ብቻ ነው ያለው ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም በዞኑ የቀቤና ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ ሙሉ የጣቢያው የጦር መሳሪያ መወሰዱ ይታወሳል። [ዋዜማ]