FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ ከሚሰሩበት የኢትዩ ሲሚኒቶ ፋብሪካ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በድንጋይ ማውጫ ካምፕ በስራ ላይ የነበሩና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱት 27 የፋብሪካው ሰራተኞች 18ቱ ሐሙስ  ዕለት መለቀቃቸውን ዋዜማ ሰምታለች ::

ከሁለት ሳምንት በፊት በታጣቂዎች ስር የቆዩት 21 ኢትጵያውያንና 6 የሕንድ ዜጎች ሲሆኑ አሁን የተለቀቁት 18 ቱ ኢትዩጵያውያን ብቻ ናቸው።

የድርጅቱ ሰራተኛ የሆኑ 6 ሕንዶች እና 3 አስተርጓሚዎች አሁንም በታጣቂዎቹ እንደተያዙ ይገኛሉ::

ሰራተኞቹ በታገቱበት ወቅት ከታጣቂዎቹ ጋር ሰራተኞቹን ለማስለቀቅ የገንዘብ ድርድር ሲያደርጉ ነበር የተባሉ 4 የኢትዩ ሲሚንቶ ሰራተኞች ደግሞ በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።

የዋዜማ ምንጮች እንደነገሩን 18ቱ  ታግተው የነበሩ ሰራተኞች ሊለቀቁ የቻሉት በአካባቢው በሚገኙ ተሰሚ ሰዎች ሽምግልና ነው ::  

በዕገታ ላይ ስላሉትና እና ከአጋቾቹ ጋር ሲደራደሩ ነበር ስለተባሉትና በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው የሚገኙት 4 የፋብሪካው ሰራተኞችን በተመለከተ ዋዜማ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አራርሳ መርዳሳ የእጅ ስልክ ላይ ደውላ ነበር። ታጋቾቹ ስለመፈታታቸው አልሰማሁም ላጣራ ካሉ በኋላ በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም  ልናገኛቸው አልቻልንም። [ዋዜማ ራዲዮ]