ዋዜማ ራዲዮ- ሶስተኛ ቀኑን የያዘውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ያስከተለውን የኢኮኖሚና የፀጥታ አደጋ እንዴት መፍታት እንደሚቻል የሀገሪቱ የደህንነት አካላት ከኦሮሚያ ክልልና ከፌደራል ሹማምንት ጋር እየተነጋገሩበት መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቆሙ።

በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥ በነዳጅና በሌሎች አቅርቦቶች ላይ ያስከተለውን ስጋት በአስቸኳይ ለመፍታት የሀገሪቱን ዋና ዋና መስመሮች ማስከፈት የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ውይይቱን ስምቻለሁ ያሉ የዋዜማ ምንጭ ነግረውናል።
አድማው በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በስፋት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ሀሞስ ከሰዓት በኋላ በማስገደድ ጭምር መለስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያደረጉ አካባቢዎችም አሉ።
አድማው የሀገሪቱን ዋና ዋና የትራንስፖርት መስመሮች በማወኩ ሳቢያ አድማው በመላ ሀገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ተፅዕኖ አድርሷል።

መከላከያ ፣ደህንነት፣ የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮና ሌሎች ባለስልጣናት ባደረጉት ምክክር አድማው ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ በመታገስ ብናልፈው ህብረተሰቡ በራሱ ጊዜ አድማው የሚያስከትልበትን ጫና መቋቋም ስለሚከብደው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ይመለሳል የሚል አስተያየት ያላቸው ባለስልጣናት መንግስት የሀይል እርምጃ ከመውስድ በመታገስ እንዲፈታው መክረዋል።
ሌሎች በበኩላቸው አድማው በሀገር ውስጥ ባለ ስውር መዋቅር የተደራጀና በዚህ በአንድ ጊዜ አድማ የሚያበቃ ስላልሆነ ወሳኝ የማጥራት እርምጃ መወሰድ አለበት የሚል አስተያየት አላቸው።
በአድማው የኦህዴድ እጅ አለበት የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩም አሉ።
በገዥው ፓርቲ ውስጥ በብአዴንና በህወሀት መካከል የተካረረው ሽኩቻ ለኦህዴድ መልካም አጋጣሚ ፈጥሎለታል ሲሉ የሚከራከሩም ነበሩ።
የመከላከያ ሰራዊትና የክልል የፀጥታ ሀይሎች ከአርብ ጀምሮ ዋና ዋና የሀገሪቱን የመንገድ መስመሮች ለማስከፈት ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ተገምቷል።
በኦሮሚያ ፀጥታ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ተጨማሪ የቁልፍ ባለስልጣናት ስብሰባ ዓርብ ዕለት ለማድረግ ዕቅድ መያዙም ተሰምቷል።