ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ለአምስት ቀናት ተጠርቶ የነበረው እቤት የመቀመጥ አድማ የተያዘለትን ግብ በመምታቱ በሶስተኛው ቀን እንዲቋረጥ መወሰኑን አስተባባሪዎቹ ገለፁ።

የአድማው አስተባባሪዎች ማንነት ይፋ ባይደረግም እንቅስቃሴውን በመወከል መረጃ በማሰራጨት ሲሰራ የሰነበተው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ስራ ኣስኪያጅ ጃዋር መሀመድ የጋራ መግለጫውን ይፋ አድርጓል።
የአድማው ዘመቻ የሚለኩ አላማዎች የነበሩት ነው ያለው መግለጫው አሳክተነዋል ያላቸውን ግቦች ዘርዝሯል።

“የመጀመሪያው፣ የኦሮሞ ትግል የራስን እድል በራስ መወሰን (Self Determination) የሚለውን ወሳኝ ግብ ሳይመታ ሊቀለበስ እንደማይችል ለስርዓቱም ሆነ ለሌሎች ግልጽ መልዕክት ለማስተለለፍ ነው። ሁለተኛው የኢኮኖሚ እድገት አምጥቻለው በሚል ስርዓቱ ያልተገባ ቅቡልነት ለማግኘት የሚያደርገውን ከንቱ ጥረት የሰዎችን የየእለት ኑሮ በማይጎዳ መልኩ ኢኮኖሚው እንዲቀዘቅዝ በማድረግ ስርዓቱ እንዲዳከምና እንዲንኮታኮት ማድረግ ነው” ይላል መግለጫው።
“ሶስተኛውና ሌለኛው ወሳኝ ምክኒያት ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት፣ በአንድ ጊዜና በሚፈልገው ጊዜ እንደሚነሳ ማሳየት፤ በዚሁም የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ህዝባዊ መሰረት ለማራጋገጥ ነው። አራተኛው የተቃውሞ አድማው መልዕክት የኦሮሞ ትግል ከእምቢተኝነት  ወደ ተቀናጀ የድል ምዕራፍ መሸጋገሩን ለማመላከት ነው” በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መግለጫ እንደሚያትተው።
“የአድማው ውጤት በሶስተኛው ቀን አጥጋቢና በ5ኛው ቀን ይጠበቅ ከነበረው ውጤትም በላይ ሆኖ በመገኘቱ፣ በዚሁ በ3ኛው ቀን በተደረገው ግምገማ መርሃ ግብሩን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዚሁ መሰረት  ከታለመው አንጻር ጊዜው ሳይጠናቀቅ በቂና አጥጋቢ ውጤት የተገኘ በመሆኑ ምክኒያት ዛሬ አድማው ከተጀመረ በ3ኛው ቀን እንዲያበቃ የቄሮ አስተባባሪዎች ወስነዋል። ስለሆነም የቤት ውስጥ መቀመጥና የግብይት አድማው ከዛሬ ነሃሴ 25፣ 2009 አመሻሽ ጀምሮ ያበቃል”  ብሏል
አድማው በገዥው ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ መወነጃጀል ያስከተለ ሲሆን መንግስት መወሰድ ያለበት እርምጃ ላይ መስማማት ተስኖት መሰንበቱ ተሰምቷል።
አድማው በኦሮሞ ወጣቶችና በባህር ማዶ ባሉ ደጋፊዎቻቸው የተደረገ መሆኑ በይፋ ቢገለፅም ኦህዴድ ይህ አድማ እንዲሳካ ተባብሯል በሚል እየተወቀሰ ነው።