PHOTO-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ጥቃት “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥም” ተብሎ መታለፍ እንደሌለበትና ስልታዊ በሆነ መንገድ የተቀነባበረ “ኦርቶዶክሳውያንን የማፅዳት ዘመቻ” ነው ብላ እንደምታምን ቤተክርስትያኒቱ ዛሬ ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

ለሀገርና አንድነትና ሰላም የሚተርፉ እሴቶችን ያበረከተችው ቤተክርስትያኗ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረ እና በተደራጀ ስልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የ‘ማጽዳት’ እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያናችን ትገነዘባለች፤ በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚኹ ከቀጠለም፣ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች ብሏል መግለጫው።


ዋዜማ የተመለከተችው መግለጫ እንደሚያብራራው ፣ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በኦሮምያ ክልል በተቀሰቀሰው የተቀነባበረ ጥቃት የክልሉ ባለስልጣናትና የፀጥታ መዋቅር ዜጎችን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማስፈንና ተጎጂዎችን በአግባቡ የመካስ ሓላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት ሲወጡ አላየሁም ብላለች ቤተክርስቲያኗ።

ቤተክርስትያኗ አደጋውን ተከትሎ 260 አባላት ያሉት አጣሪ ቡድን አቋቁማ በስድስት አህጉረ ስብከት የሚገኙ 25 ወረዳዎች በማሰማራት የጉዳቱን መጠንና ሁኔታ መረጃ አሰባስባለች።

አጣሪው ቡድን ተጎጂዎችንና በማነጋገር እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ባቀረበው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነት እና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኀይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዒላማ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ አረጋግጫለሁ ብላለች ቤተክርስቲያኗ።


ከሰኔ 22 ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በዚያ ጥቃት፥ ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፤ 38 ምእመናን ቋሚ(ከባድ)፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከሰባት ሺሕ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር፣ በተለያየ ደረጃ ለሚገለጽ ሥነ ልቡናዊ እና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ ከአምስት ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን፣ ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከረፈደም ቢሆን መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተክርስቲያኗ ጠይቃለች።

መንግስት በተሳሳቱ ትርክቶች መነሻነት በቤተክርስቲያኗና በምዕመናን ላይ እየተባባሰ የመጣውን ኾነ ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሣቀቅ እና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን፣ ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስ እና በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጣ ቤተክርስቲያን በአጽንዖት ታሳስባለች፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቤተክርስቲያኗና በምዕመናን ላይ የተባባሰውን ጥቃት ለማስቆምና አጥፊዎችንም በህግ ለመጠየቅ ከክልል መንግስታት ጋር የተደረጉ ውይይቶች ገንቢ እንደነበሩ ቢስማማም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወቅቱ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት ክፍተቶች እንዳሉበት የሚያምኑ መሪዎች መኖራቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቅሰዋል። ይህን ልዩነት በአደባባይ ከመግለጽ ለመቆጠብ መወሰኑን ዋዜማ ተረድታለች።

ምዕመናንም በአሁኑ ወቅት በአስቸጋሪ መልኩ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ጭምር ተጋፍጠው ያሉ ተጎጂዎችን በመርዳትና በመደገፍ በአንድነት እንዲቆሙ ቤተክርስቲያኗ ጠይቃለች። [ዋዜማ ራዲዮ]

——–

ማስታወሻ፤ ቀደም ባለው የዚህ ዜና አይነቴ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋራ ያላት ግንኙነት በመግለጫው እንደተካተት ተጠቅሶ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ አለመካተቱን፣ ሆኖም ውይይት እንደተደረገበት በመረዳታችን ዜናው በዚሁ መንፈስ ተስተካክሏል።