eac-logoዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የፖለቲካና የስብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ገለፃ የሚደረግበት ጉባዔ በቅርቡ ይደረጋል።
የኢትዮጵያና አሜሪካ ምክር ቤት(Ethiopian American Council)  የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው በዚሁ ጉባዔ ላይ የፖለቲካ መሪዎች የስብዓዊ መብት ተሟጋቾች ምሁራንና የመገናኛ ብዙሀን ይሳተፋሉ።
የአሜሪካ መንግስት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተወካዮች፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት፣ የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተወካይና ሌሎች ከፖሊሲ ማውጣት ጋር የሚሰሩ እንግዶች ተጋብዘዋል።
ከዚህ ቀደም ምርጫ 97 ተከትሎ በአሜሪካ ኮንግረስ የኢትዮጵያን መንግስት አደብ ለማስገዛት ያለሙ ረቂቅ ህጎች እንዲወጡ መሪነቱን የወሰደው ካውንስሉ በዚህኛው ጉባዔ በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ውይይትና የመፍትሄ ሀሳብ ይቀርባል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ አዘጋጆቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ጉባዔው በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ቅፅር በካሊፎርኒያ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር ጃንዋሪ 21 እና 22 የሚካሄድ መሆኑን አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል።
የምስራቅ አፍሪቃ የፀጥታ ጉዳይና የኢትዮጵያ ሚና፣ የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደተሻለ የዴሞክራሲ መንገድ ለመውሰድ ምን እርምጃ መወሰድ አለበት? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ተናጋሪዎች ሀሳብ አቅርበው ውይይት ይደረጋል።