HIV Testingአገሪቱን ከጫፍ ጫፍ አካሎ 134 ሺህ ሰዎችን ህይወት ለመንጠቅ ሁለት አስርቶችን ብቻ የወሰደው የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገኘ በይፋ ከተነገረ ዘንድሮ 30ኛ ዓመቱን ደፍኗል። በነዚሁ ዓመታት ከ744 ሺህ በላይ ህፃናትን ያለወላጅ አስቀርቷል ይላል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከብሔራዊ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት ጋር በጋራ ያወጡት “ኤድስ በኢትዮጵያ 2014” የተባለ ሪፖርት።

[ሰላም መኩሪያ ያዘጋጀችውን መስሉ ንጉስ ታቀርበዋለች አድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

በኢትዮጵያ የስርጭቱ ፍጥነት ጣሪያ የነካው በ1988 ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ በዚሁ ዓመት ከ166 ሺህ በላይ ሰዎች ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጋልጠዋል። በያዝነው አመት ታህሳስ ወር የብሔራዊ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት ያወጣው ሪፖርት ምንም እንኳን የስርጭቱ ፍጥነት በአገር አቀፍ ደረጃ ለተወሰኑ አመታት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም በ2007 ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ቁጥር 741 ሺህ ነው ይላል። ከዚህ ቁጥር 61 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

በአገሪቷ የተሰፋፋው ኤች አይ ቪ ስርጭት በሴቶች የሚበረታ እንደሆነ የሚገልፀው ይኸው ሪፖርት 1.4በመቶ በአገሪቷ ባሉ ሴቶች የታየው የስርጭት በዛት በወንዶች ቀንሶ 0.8 በመቶ ነው፡፡
ከ15 -19 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች 0.2 በመቶዎቹ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ የሚያስረዳው ይህ ሪፖርት በተመሳሳይ የእድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶች ተጋላጭነታቸው ዜሮ ነው፡፡ በወጣትነት እድሜም ቢሆን በሴቶች የሚጎላው የቫይረሱ ስርጭት ከ25- 29 የእድሜ ክልል ያሉ ወጣት ሴቶች 2.9 በመቶዎቹ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ሲረጋገጥ በተመሳሳይ እድሜ በወንዶች የታየው ስርጭት መጠን 0.9 በመቶ ነው።

ከ15-49 ዕድሜ ክልል በሚገኙ አዋቂ ወንዶችና ሴቶች ላይ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ስለመምጣቱ የሚመሰከረው ይኸው ሪፖርት በዚሁ እድሜ ክልል በ2006 ዓ.ም 1.15 በመቶ የነበርው ስርጭት ስፋት በ2007 ወደ 1.22 መጨመሩን ይገልፃል፡፡ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ቁጥር ያለማቋረጥ እንዲጨምር በዋንኛነት ሪፖርቱ ምክኒያት ነው ያለው ስለ ኤች አይ ቪ ሁለገብ እውቀት በበቂ ሁኔታ አለመዳረስን ነው፡፡

ኤች አይ ቪን በተመለከተ በቂ የሚባል ግንዛቤ እና እውቀት ያለቸው ሴቶች ከጠቅላላው ቁጥራቸው 19 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፣ ኮንዶምን ሁልጊዜ እና በአግባቡ አለመጠቀም ብዙዎችን ለቫይረሱ ተጋላጭ አድርጓል። በሴተኛ አዳሪዎች ያለዉ የቫይረሱ ስርጭት 25 በመቶ ደርሶ አሁንም ግብረስጋ ግንኙነት ከሚፈፅሙ ወንዶች መካከል 64 በመቶዎቹ ሴተኛ አዳሪዎችን ይጎበኛሉ።

“ኤች አይ ቪ መልሶ ሊያገረሽ ወደማይችልበት ደረጃ አልወረደም” የሚለው ሪፖርቱ፣ ወጥ የኮንዶም ማሰራጨት አሰራር አለመዘርጋት እና የማሰራጫ ጣቢያዎች የክትትል ስርዓት አለመኖር ችግሩን በበቂ መንገድ መከላከል እንዳይቻል እንዳደረገ ይናገራል።

[በኮንደም አጠቃቀም ዙሪያ ያነጋገርናቸው ወጣቶች አስተያየት እዚህ አድምጡት]

በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምርመራ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆን እና የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት ከሚያስፈልጋቸው ለ13 በመቶዎቹ ብቻ መድረስ የቫይረሱን ቁጥር ለመጨመር እንደ ምክንያት ናቸው። ህፃናት ከእናታቸው ኤች አይ ቪ ቫይረስ እንዳይወረሱ ማድረግ የተቻለውም ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች መካከል 0.8 በሞቶዎቹን ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የ2007 ጥናታዊ ትንበያ የኤች አይ ቪ ስርጭት ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከማህበረሰብ ማህበረስብ ይለያያል፡፡ የስርጭት ቁጥሩ አነስተኛ ሆኖ የተመዘገበው ደቡብ ሕዝቦች እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ከጠቅላላ ህዝባቸው 0.7በመቶዎቹ ቫይረሱ እንደሚገኝባቸው ቁጥሮቹ ሲያስረዱ ይህ ቁጥር ልቆ በጋምቤላ 5.03 በመቶ እየመራ ይገኛል፡፡

ከጋምቤላ ቀጥሎ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የሚያስቀምጠው የስርጭት መጠኑ፣ ከገጠር ይልቅ በከተማ ቫይረሱ በሰፊ ልዩነት ተስፋፍቷል፣ በአገሪቱ በከተማ ውስጥ ከሚገኙ ነዋሪዎች በቫይረሱ ስርጭት ብዛት ቅድሚያውን የያዙ የክልል ከተሞች የሚገኙት በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ነው።

ቫይረሱ በሰፋት ከተሰራጨባቸው ከተሞች መካከል የምተገኘው አዲስ አበባም፣ በከተማዋ ውስጥ ከሚኖሩ አዋቂዎች 11 .7 በመቶዎቹ ኤች አይ ቪ በደማቸው አለ፡፡ የኤችአይቪ ስርጭት ከዋና የአስፋልት መንገድ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ያለዉ ስርጭት ከዛ በራቀ ከሚኖሩት አንፃር በአራት ዕጥፍ ከፍ ያለ እንደሆነ ሪፖርቱ አስታውቋል።