Protestors in Ataye after days of conflict- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ከመጋቢት 24 እስከ 29 2011 ዓም በሰሜን ሸዋ ዞን እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮምያ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ በተለይም በከሚሴ ፣ በአጣዬ ፣ ማጀቴ ቆሬ ሜዳ እና አጎራባች ወረዳዎች በተነሳ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ እና ንብረት መውደሙ የሚታወስ ነው፡፡

ይህንን ተከትሎም ምርመራ ሲያደርግ የቆየው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በ2011 ዓም ማገባደጃ ሀምሌ ወር ላይ ደሴ በሚገኘው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍረድ ቤት በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል ያላቸውን 38 ግለሰቦች ከሷል፡፡

ሆኖም ተከሳሾች ጉዳያቸው በአዲስ አበባ ማለትም በፌደራል ፍርድ ቤት እንዲታይላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡

ይህንን የመወሰን ስልጣን ያለው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍረድ ቤት እንዲታይ በወሰነው መሰረት አራቱ የክስ መዝገቦች በድጋሜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ እና 20ኛ ወንጀል ችሎቶች ተከፍተው መተያት ጀምረዋል፡፡

አቃቤ ህግ በክሱ በድምሩ የ80 ሰው ህይወት ያለፈ ስለመሆኑ እና በርታ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው አካቷል፡፡

በተጨማሪም 1 ቤተክርስቲያን የተቃጠለ መሆኑን እና ይህም ግምቱ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ሌሎች የወደሙ የአካባቢው ንብረቶችም እንደነበሩ ጨምሮ ገልፅዋል

በአራት መዝገብ ተከፋፍለው እና በተለያየ ቀጠሮ እየታዩ ያሉት ተከሳሾቹም በበኩላቸው በክሱ የተዘረዘረው የወንጀል ዝርዝር የተጠቀሱባቸውን የህግ ድንጋጌ የሚያሟሉ አይደሉም ሲሉ የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያቸውን አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የስነ ስርአት ህጉ በሚያዘው መሰረት የወንጀል ተሳትፎ ድረሻ ተሟልቶ አልቀረበም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

አቃቤ ህግ በመቃወምያዎቹ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ትእዛዝ የተሰጠ ሲሆን ችሎቶቹ ከየካቲት 24 ጀምሮ በመቃወምያ ክርክሩ ላይ በሚኖሩ ተከታታይ ቀጠሮዎች ብይን ለመስጠት ቀጥረዋል፡፡