• ጋዜጠኞች ጨረታውን እንዳይዘግቡ ለመከልከል ተሞክሯል፡፡
  • አሜሪካን ግቢ ለድጋሚ ጨረታ የቀረቡ ሦስት ቦታዎች ባልታወቀ ምክንያት ተሠረዙ
  • ቂርቆስ 1ሺህ ካሬ ቦታ በ63 ሚሊዮን ብር ተሸጧል

The Municipality ዋዜማ ራዲዮ- በርካታ ዉዝግብና ግርግር ያስተናገደው የ26ኛው ዙር የአዲስ አበባ የመሬት ግብይት ከዓድዋ የድል በዓል በፊት በነበሩ ሁለት ተከታታይ ቀናት በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ተከፍቷል፡፡ ሰባት ክፍለ ከተሞችን ባሳተፈው በዚህ ዙር የመሬት ጨረታ ከፍተኛ የሚባሉ ዋጋዎች ቢቀርቡም ባልተለመደ ሁኔታ ደግሞ ዝቅ ያሉ ዋጋዎችም የተሰሙበት ነበር፡፡

በ24ኛው ዙር ላይ የከተማዋን የሊዝ ክብረወሰን በሰበረ ዋጋ ተሸጠው ነገር ግን አሸናፊዎቹ ሳይወስዷቸው የቀሩ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ አንድ፣ አሜሪካን ግቢ የሚገኙ ሦስት ቦታዎች በዚህ ዙር ለድጋሚ ጨረታ እንደወጡ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ከተገለፀ በኋላ ጨረታው ሊከፈት አንድ ቀን ሲቀረው ባልታወቀ ምክንያት ተሰርዘዋል፡፡ ከነዚህ መሐል ለካሬ 355ሺህ 500 ብር ቀርቦበት ግማሽ ቢሊየን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ተሸጦ የነበረው ቦታ ይገኝበታል፡፡

26ኛው ዙር ጨረታ ሊከፈት አንድ ቀን ሲቀረው እነዚህ ሦስት ቁልፍ ቦታዎች ብቻ ተለይተው መሠረዛቸው ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ክስተቱ ጨረታውን ለሚከታተሉ ገለልተኛ ታዛቢዎችም ቢኾን እንግዳ ነው የኾነባቸው፡፡ ምናልባት መንግሥት የጨረታ ዋጋ በተቀዛቀዘበትና ገንዘብ እምብዛምም በማይዘዋወርበት ወቅት ቦታዎቹን ለጨረታ ማቅረቡ በዝቅተኛ ዋጋ ሊሸጡብኝ ይችላሉ ከሚል ስጋት የተነሳ ሰርዟቸው ሊኾን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል፡፡

በሊዝ የሚሸጡ ቦታዎች ከፍተኛ የበጀት ቀውስ ለሚገጥመው የአዲስ አበባ መስተዳደር እንደ ሁነኛ ድጋፍ እንደሚያገለግለው ይታወቃል፡፡ ከሊዝ ክፍያ የሚገኘው ገቢ ወሳኝ በመኾኑ በሊዝ አሠራር ድርብ ወለድ ማስከፈል  ሕጋዊ መሠረት በሌለው ሁኔታ ከሌሎች ክልሎች በተለየ የአዲስ አበባ መስተዳደር  የሊዝ መሬት አሸናፊዎች በየዓመቱ ድርብ ወለድ እንዲከፍሉ የሚያስገድ አሰራርን ይከተላል፡፡ ይህም የኾነው  በዋናነት በጀቱ በዚሁ የሊዝ ክፍያ የሚደጎም በመሆኑ  ነው፡፡  ለምሳሌ በየዝነው በጀት ዓመት መስተዳደሩ ከሰበሰበው 15 ቢሊየን ብር ዉስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው ከሊዝ ኪራይ  የሚሰበሰበው ዓመታዊ የሊዝ ክፍያ ነው፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተሰረዙትን ሦስት የአሜሪካን ግቢ ቦታዎች ሳይጨምር 10 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡ ዊንጌት አካባቢ ስፋታቸው ከ500 እስከ 600 ካሬ የሚሰፉ 8 ቦታዎች ከ7ሺህ እስከ 13ሺህ ብር በኾነ ተመጣጣኝ ዋጋ ተሸጠዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከቀረቡ 13 ቦታዎች ሰባት የሚኾኑት በቂ ተጫራች አለማግኘታቸውም የዙሩ አስገራሚ ክስተት ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከቀረቡ 270 ቦታዎች ዉስጥ 14ት ቦታዎች ተጫራች አላገኙም፡፡  በአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ተጫራች ማጣት እምብዛምም የተለመደ አይደለም፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ በወረዳ 4 የቀረቡ 6 ቦታዎች ከ8ሺህ እስከ 12ሺህ ብር ቀርቦባቸው ባልተጋነነ ዋጋ መሸጣቸውም ለብዙዎች ተስፋን ሰጥቷል፡፡

Bole Bulbula Areal viewበየካ ክፍለ ከተማ ከቀረቡ 9 ቦታዎች ዉስጥ አያት፣ ልዩ ስሙ ክብረ ደመና ቤተክርስቲያን አካባቢ የቀረበች ጠባብ መሬት የብዙ ተጫራቾችን ትኩረት ስባለች፡፡ በዋጋ ደረጃም የዙሩን ትልቅ ዋጋ አስመዝግባለች፡፡ ይህቺ 105 ካሬ ብቻ ስፋት ያላት ኪስ ቦታ ከ90 በላይ ተጫራቾች የተራኮቱባት ሲኾን ፡፡ ወይዘሮ ዓለሚቱ መንግስቱ ለካሬ 43ሺህ 150 ብር በማቅረብ ቦታዋን የግላቸው ሲያደርጉ አቶ ጀማል ደምሴ የተባሉ ግለሰብ 33ሺህ ብር ለካሬ አቅርበው 2ኛ ኾነዋል፡፡

ወይዘሮ ዓለሚቱ 105 ካሬ የኾነ ጠባብ ቦታን ለመግዛት በድምሩ 4.5 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ ገንዘብ በተራዘመ ጊዜ የሚከፈል ቢኾንም፡፡ ይህ ዋጋ ታዲያ በየዓመቱ ታሳቢ የሚደረገውን ከፍተኛ የወለድ ምጣኔን አያካትትም፡፡

የመሬት ጨረታን የሚከታተሉ ታዛቢዎች የወይዘሮዋ የተጋነነ ዋጋ ለዚህ ጠባብ መሬት ለምን እንደቀረበ ማስረዳት ይከብዳቸዋል፡፡ ምክንያቱም የዚህን ቦታ እጥፍ የሚኾን ስፋት ያለው ቦታ በተመሳሳይ ሰፈር እና ኹኔታ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ማግኘት የሚቻል መኾኑን መረዳታቸው ነው፡፡ ምናልባት አካባቢው በጥሩ ኹኔታ የለማና መሠረተ ልማት የተሟላለት መኾኑ፣ ወይም ደግሞ ባለሐብቷ ለሰፈሩ ልዩ ፍቅር ካላቸው ለቦታው የተሰጠው ዋጋ ስሜት ይሰጥ ይሆናል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

በዚሁ የካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 13፣ አያትና ወረዳ አንድ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የቀረቡ 9 ቦታዎች ብዙዎቹ ለካሬ ከ7ሺህ እስከ 15ሺህ ብር የሚጠጋ ዋጋ ቀርቦባቸው ተጠናቀዋል፡፡

ልደታ ክፍለ ከተማ ለዚህ ዙር ያቀረባቸው ሁለት ቦታዎች ብቻ ሲኾኑ ሁለቱም ከዚህ ቀደም ለጨረታ ቀርበው ዉድ ዋጋ ቀርቦባቸው በአሸናፊዎቹ ሳይወሰዱ የቀሩ ነበሩ፡፡ በዚህኛው ዙር ብስራተ ኤፍ ኤም ጣቢያ አካባቢ፣ ወረዳ 10 አፍሪካ ኅብረት ማዶ የሚገኘውና 978 ካሬ የሚሰፋው ቦታ አራት ተጫራቾች ብቻ ቀርበውበት ሁለቱ መታወቂያቸውን ከጨረታ ሰነድ ጋር ባለማያያዛቸው ጨረታው ተሰርዞባቸዋል፡፡ የተቀሩት ሁለቱ ያቀረቡት ዋጋም ዉድቅ ኾኗል፡፡ ምክንያቱም ለአንድ ጨረታ በትንሹ ሦስት ተጫራቾች መቅረብ ስላለባቸው ነው፡፡

በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አፍሪካ ኅብረት አካባቢ 1ሺህ 95 ካሬ ስፋት የነበረው ቦታ 5 ተጫራቾች ብቻ ቀርበውበት አምድይሁን ጄኔራል ትሬዲንግ ለካሬ 57ሺህ ብር በማቅረብ ቦታውን በ62 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ ዋጋ በመግዛት የግሉ አድርጎታል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ የቀረቡ ሁለት ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ቡልጋሪያ አካባቢ የአፍሪካ ኅብረት ጀርባ 1354 ካሬ የሚሰፋ ቦታ ዱናአብ ትሬዲንግ ለካሬ 59ሺህ ብር በማቅረብ ቦታውን በ80 ሚሊዮን ብር ጠቅልሎ  የግሉ ማድረግ ችሏል፡፡

በተመሳሳይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከገነት ሆቴል ወደ ቄራ በሚወስደው ዋና መንገድ የሚገኝና ለረዥም ጊዜያት ቆሻሻ መድፊያ ኾኖ ያገለግል የነበረ 1028 ካሬ ቦታ የዙሩ ከፍተኛ ዋጋን በማግኘት ተሸጧል፡፡ አቶ ናስር ጀማል የተባሉ ባለሐብት ለካሬ 61ሺ130 ብር ሲያቀርቡ ወይዘሮ ማርነሽ ፍቃዱ የተባሉ ሌላ ባለሐብት ደግሞ 61ሺ 155 ብር በማቅረብ ተቀራራቢ ፉክክር አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ ወይዘሮ ማርነሽ ለካሬ ከፍተኛውን ዋጋ ቢያቀርቡም አቶ ናስር ጀማል የጠቅላላ ዋጋውን 30 በመቶ ቀድሜ ለመስተዳደሩ ገቢ አደርጋለሁ በማለታቸው አሸናፊ ተደርገዋል፡፡ የዚህ ለአካባቢው ቆሻሻ መድፊያ ኾኖ ያገለግል የነበረ ስፍራ ጠቅላላ ዋጋ ግዢ 62 ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡

ኮልፌና ንፋስ ስልክ

ከትናንተ በስቲያ ማክሰኞ ማለዳ ሦስት ሰዓት ላይ የተከፈተው ጨረታ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ቆይቶ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ለንፋስ ስልክና ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ጨረታ የገቡ ፖስታዎች በተከፈቱበት የትናንት በስቲያው ዉሎ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 3 አየር ጤና ረጲ አካባቢና ወረዳ 7 ዓለም ባንክ አካባቢ የሚገኙ 25 ቦታዎች ከ15ሺህ እስከ 34ሺ የሚጠጋ  ዉድ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ኮልፌ ቀራንዮ ዓለም ባንክና ቤቴል አካባቢ ለሚገኙ መሬቶች ወትሮም ከፍተኛ ዋጋ ስለሚቀርብባቸው የዋጋዎች መናር ብዙዎችን አላስገረመም፡፡

ከዚያ ይልቅ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ሐና ማርያም ማንጎ አንድና ሁለት ሰፈር የቀረቡ 8 ቦታዎች የዙሩ ዝቅተኛ ዉጤቶች ይመዘገቡባቸዋል የሚል ግምት ተሰጥቷቸው የነበረ ቢኾንም የተጠበቀውን ያህል ዝቅ ያለ ዋጋ ሳይቀርብባቸው ቀርቷል፡፡ ይህ ግምት የተሰጠው አካባቢው ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ያልተሟላለት መኾኑ ሲኾን ሕገ ወጥ ግንባታ ተካሄዶበት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ደም አፋሳሽ በኾነ መልኩ በግብረ ኃይል የፀዳ ሰፈር መኾኑም የብዙ ተጫራቾችን ቀልብ ላይስብ ይችላል ወደሚል ድምዳሜ እንዲኬድ አድርጓል፡፡

ኾኖም በዚህ ስፍራ የቀረቡ 10 ቦታዎች ስፋታቸው ከ250 እስከ 400 ካሬ የኾነና አገልግሎታቸው ለቅይጥ እንደሆነ የተመለከተ ሲኾን ሁሉም ለካሬ ከ5ሺህ እስከ 11ሺህ ብር ቀርቦባቸዋል፡፡ የዙሩ ዝቅተኛ ዋጋ የተመዘገበውም በዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ለመጫረት በርከት ብለው የሄዱ ባለሐብቶች በአካባቢው ተፈናቃይ ጎረምሶች ዛቻና ማስፈራሪያ ይቀርብባቸው እንደነበር የዓይን እማኞች ለዋዜማ ሪፖርተር ነግረዋታል፡፡ “ደማችን በፈሰሰበት መሬት ፎቅ ስትሰሩ ቆመን አንመለትም” የሚሉ ንግግሮችን ከነዋሪዎች መስማታቸው ከጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንደገታው የተናገሩ አንድ ባለሐብት ቦታውም ቢኾን ወደ ልማት ለመግባት የሚጋብዝ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሐናማርያም ማንጎ በፈጣኑ የአዳማ መንገድ በኩል የሚዋሰን በአመዛኙ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ሲኾን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካል ኾኖ ቆይቷል፡፡ ስፍራው ባለፈው ዓመት ሕገ ወጥ ግንባታ አካሄደዋል በሚል አስራ አንድ ሺህ ቤቶች የፈረሱበት ተራራማ አቀማመጥ ያለው ሲኾን ምንም ዓይነት መንገድ ያልተበጀለትና ከመደበኛ መሠረተ ልማት የራቀ የጭቁኖች ሰፈር ነው፡፡

ያልተጫረተ አይገባም

እስከዛሬ በተካሄዱ የመሬት ግብይቶች ባልተለመደ ሁኔታ ተጫራቾች የመጫረቻ ሰነዶቻቸውን እንዲያባዙና በሦስት ፖስታዎች አሽገው እንዲያቀርቡ የተገደዱትም በዚሁ እንቅፋት በበዛበት ዙር ነው፡፡ ይህ ትዕዛዝ የመጣው በድንገት ሲኾን የአሰራር ለውጥ መኖሩ የመጫረቻ ሰነድ ላይም ኾነ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ሳይገለጽ ነው፡፡ የጨረታው ማስገቢያ ዕለት በማዘጋጃ ቤት ሰነድ መግዣ ቢሮ ዋናው በር ላይ በተለጠፈ ብጫቂ ማስታወቂያ ብቻ የአሰራር ለውጥ መደረጉ ለሙስና በር የሚከፍት እንደሆነ ብዙዎች ሲገልፁ ነበር፡፡ እንዴት መሬትን የሚያህል ነገር እየሸጥክ እንዲህ ዓይነት ዝርክርክ አሰራር ትከተላለህ?” ያሉ ባለሐብት ጉዳዩን ወደ ፀረ ሙስና እንደሚወስዱት ሲዝቱ ተሰምተዋል፡፡

የግድግዳ ማስታወቂያውን ባለማየት በተለመደው አሰራር ሰነዳቸውን ያስገቡ በርካታ ተጫራቾች ሰነዳቸው ዉድቅ መደረጉ ሲነገራቸው ተቃውሟቸውን በአዳራሹ ገልጠዋል፡፡

የጨረታ ሂደቱ ላይ ምንም ለውጥ እንደሌለ በማሰብ በተለመደው አሰራር አንድ ፖስታ ብቻ በመጠቀም ሰነዳቸውን አሽገው በሳጥኑ ዉስጥ ያስገቡ 66 የሚኾኑ ተጫራቾች ከዉድድር ዉጭ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎቹ አሰራሩን በመቃወም አቤቱታቸውን በጽሑፍ ለማቅረብ የለማ መሬት ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት አካባቢ ተሰባስበው ሄደዋል፡፡  አቤቱታቸው ተቀባይነት ካገኘ ምናልባት የ26ኛው ዙር ጨረታ ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ የሚችልበት አግባብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ ጨረታው በሚከፈትበት ማለዳ ተጫራቾችና ሕጋዊ ወኪሎቻቸው ካልሆኑ ጋዜጠኞችም ኾኑ ጨረታውን ለመታዘብ የመጡ በሙሉ አዳራሽ ዉስጥ እንዳይገቡ ሙከራዎች የተደረጉ ሲኾን የሰው ቁጥር እየበረከተ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ቁጥጥሩ እንዲቀር ኾኗል፡፡

የጨረታ ዉጤቱን የመግለጽ ሂደት ነገ አርብና በመጪው ሰኞ የሚቀጥል ሲኾን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9፣ 10 እና 11 ጎሮ፣ ሰሚትና አያት የሚገኙ 94 ቦታዎች ዉጤት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡