FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ በምገባ ፕሮግራም ስር ባለ በትምህርት ቤት በተፈጠረ “የምግብ መመረዝ” ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በተለያዩ ሆስፒታሎች ዛሬ ህክምና ሲደረግላቸው ውሏል።


ጥይት ፋብሪካ አቅራቢያ የሚገኘው ፍሬሕይወት ቁጥር አንድ አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቁርስ ከበሉ በኋላ በመታመማቸው ወደ ዘውዲቱ ፣ ጥቁር አንበሳና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ተወስደው ህክምና ሲደረግላቸው መዋሉን የዋዜማ ሪፖርተር ተከታትሏል። ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ጉልኮስ ተሰቷቸው እስከ 10 ሰአት ሆስፒታል ቆይተው ወደቤታቸው ሄደዋል፡፡


የዋዜማ ሪፖርተር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያነጋገራቸው ተማሪዎች “እስከዛሬ የምንበላው የኦቾሎኒ ቅቤ በዳቦ ነበር ዛሬ ግን ማርማራት በዳቦ ከበላን በኋላ በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ብዙ ተማሪዎች ታመምን” ያለው የ5ተኛ ክፍል ፍሬህይወት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ “አንቡላንስ መቶ መጀመሪያ ጤና ጣቢያ ወሰደን እዛ ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ወደ ጥቁር አንበሳ አመጡን” ብሏል፡፡


የዋዜማ ሪፖርተር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ 100 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ህክምና እየተደረገላቸው አይቷል፡፡ ህክምና ሲሰጡ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ልጀቻንን መንግስት እመግባለው ሲል ካለብን ችግር አንፃር ደስተኞች ነበርን ፣ ገና ከተጀመረ ሁለት ወሩ ነው ሲቆይ ከዚህ የባሰ ሊከሰት ይችላል። ጤነኛ ልጅ ልከን 4 ሰአት ላይ ታመመ ስንባል በጣም ይረብሻል መንግስት ምን እንደተፈጠረ በግልፅ ለህብረተሰቡ ግልፅ መናገር አለበት ይላሉ ስሜን ሸሽጉልኝ ያሉ ወላጅ ።


በዘውዲቱ ሆስፒታል በስራ ላይ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ወደ 40 ሚጠጉ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል መጥተው የመጀመሪያ ህክምና ተደርጎላቸው እንደተመለሱ ለዋዜማ የተናገሩ ሲሆን ተማሪዎቹ ትውከት እና መንቀጥቀጥ ነበራቸው ብለዋል ፡፡
የሁሉም ተማሪዎች ህመም አንድ አይነት ነበር ያሉት የጤና ባለሙያዎቹ በብዛት ስላስመለሱ አቅም አንሷቸው ስለነበር ግሉኮስ ተሰቷቸው ወደ ቤታቸው ሄደዋል፡፡
“የምግብ መመረዝ አይደለም ማለት አይቻልም- የሁሉም በሽታ አንድ አይነት ነው፡፡ ከ6 አመት ጀምሮ እስከ 15 አመት የሚሆኑ ተማሪዎች በሆስፒታሉ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተዋል የከፋ የሚባል ጉዳት ባይደርስባቸውም ህፃናቶች በጣም ተረብሸው ነበር” ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል ፡፡


መንግስት የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ችግረኛ ተማሪዎችን በቀን ሁለቴ ቁርስ እና ምሳ እንደሚመግብ ይታወቃል፡፡
አዲስ አበባ መስተዳድር በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ እየተጠበቀ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]