ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት እና መሬት ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የታዩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ ታግደው የነበሩ የግንባታ ፍቃድ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ መወሰኑን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ኢትዮጵያ በገባችበት ጦርነት ሳቢያ ለተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ተጋልጣለች በሚል መንግስት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ሲጥል መቆየቱ ይታወሳል።በተለይ በአዲስ አበባ ህገ ወጥ የመሬት ሽያጭ በመብዛቱ የግንባታ ፍቃድ የመስጠትና ከቤት ሽያጭና ስም ማዞር ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ህገወጥ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑና እንዲሁም የተገልጋዮች ጥያቄም በማየሉ የተወሰኑት የግንባታ ፍቃድ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ስጦታው አካለ ለዋዜማ ራዲዮ ተናግረዋል።

የግንባታ ማስጀመሪያ  ፍቃድ መስጠት ፣የእድሳት ፍቃድ ፣ የህንጻ መጠቀሚያ ፍቃድ ፣ በሊዝ ይዞታዎች አዲስ የግንባታ ፈቃድ የመስጠት ፣ ለነባር ይዞታዎች የግንባታ ማሻሻያ አገልግሎት እንዲጀመሩ ከተወሰነላቸው አገልግሎቶች መካከል እንደሚገኙም ማረጋገጥ ችለናል።

ሆኖም ሁሉም አይነት የግንባታ ፍቃድ አገልግሎቶች አለመጀራቸውንም አቶ ስጦታው ነግረውናል። የተፈቀዱት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የተወሰነበትት ደብዳቤም ለሚመለከታቸው አስፈጻሚ ተቋማት የተሰራጨ መሆኑንም ሰምተናል።

 የተወሰኑት የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቶች መጀመር በአዲስ አበባ ከተማ ተቀዛቅዞ የቆየውን የግንባታ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ቢሆንም ለዳግም መሬት ወረራ በር እንዳይከፍት አሁንም ስጋት አለ።

መንግስት ሀገሪቱ ለኢኮኖሚ አሻጥሮች ተጋልጣለች በሚል እገዳ ጥሎባቸው የነበሩ እንደ የባንክ ብድር ያሉ ገደቦችን ያነሳ ሲሆን ከቤት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተጣሉ ገደቦች ግን እስካሁን አልተነሱም። [ዋዜማ ራዲዮ]