በአዲስ አበባ የመሬት የሊዝ ጨረታ በይፋ ከተቋረጠ በርካታ ወራት ቢቆጠሩም አሁንም ህግን ባልተከተለ መንገድ መሬት እየተከፋፈለ ነው።

Takele Uma- Deputy Mayor of Addis Ababa

ዋዜማ ራዲዮ- ያለፉት ጥቂት ሳምንታት በአዲስ አበባ የመሬት ቅርምቱ እጅጉን ተጧጡፎ የቀጠለበት ሆኗል። አንዳንዶቹ የመሬት ቅርምቶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኒ የወሰነውን ውሳኔ አስታከው የተሰሩ መሆናቸውንም አስተውለናል።

ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ፥ የከተማ አስተዳደሩ በ2003 አ.ም ማለትም ኩማ ደመቅሳ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ የተሰጣቸውን መሬት አላለሙም በሚል በርካታ ባለሀብቶች የተቀሙት መሬት እንዲመለስላቸው ተወስኖ ነበር። ሆኖም ይህ ውሳኔ ከጅምሩም በችግር የተሞላ ነው። ምክንያቱም ባለሀብቶቹ መሬቱን ለምን ተቀሙ ? በምን መልኩስ ይመለስላቸው? የሚለው ሊጣራ ይገባ ነበር። ሆኖም ካቢኔው በዚህ ላይ በቂ ምክክር ያደረገ አይመስልም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታድያ መሬቱን የመመለሱ ሂደት ከፍተኛ ችግር የተስተዋለበትና ለአድልዎና ሙስና የተጋለጠ ሆኗል።


መሬቱ ሲከፋፈል ቀድሞም ቢሆን ያልተነጠቁና ውሳኔው የማይመለከታቸው ሰዎች ተካተውበታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ውሳኔው የሚመለከታቸው ቢሆኑ ቀድሞ የተነጠቁት መሬት ሊመለስላቸው ሲገባ ፣ ያም ካልሆነ አማራጮችን ማየት እየተቻላ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ቦታዎችን ወደ ማከፋፈል ተገብቷል

ከሰሞኑ ካዛንቺስና ቦሌ አካባቢዎች በሰፊው እየተሰጠ ያለው መሬት የዚሁ ቅርምት አካል እንደሆነም ምንጮቻችን ያብራራሉ። ለአረንጓዴ ቦታነት ተከልለዋል የተባሉ ቦታዎች ሳይቀሩ ግልጽነት በጎደለው መልኩ እየተሰጡ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2009 አ.ም ለኳታር ባለሀብቶች ሰጥቶት ያልለማውንም መሬት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መስጠቱን ዋዜማ ራድዮ ሰምታለች። ኢዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ የተሰኘው የኳታር ባለሀብቶች ስብስብ አፍሪካ ህብረት አቅራቢያ ነበር 60 ሺህ ካሬ ስፋት ያለውን መሬት የወሰደው። በስፍራውም ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ፣ የመኖርያ ቤቶችና የገበያ ማእከል ሊገነባ ነበር መሬቱን የተረከበው። ሆኖም በ350 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ይከናወናል የተባለው ፕሮጀክት የውሀ ሽታ ሆኖ ቆይቷል።

ለዚህ የኳታር ባለሀብቶች ቡድን በልዩ ሁኔታ መሬት ሲቀርብለት በስፍራው የነበሩ ነዋሪዎች ያለ ምንም በቂ ዝግጅት በጥድፊያ ነበር እንዲነሱ የተደረጉት። ይህ ሁሉ ሆኖም ፕሮጀክቱ አልተሰራም ፣ መሬቱም ነዋሪዎች በፍጥነት እንደመፈናቀላቸው ሳይሆን ታጥሮ ነበር ለአመታት የተቀመጠው።

ለኳታሮቹ ባለሀብቶች ሽሽት ከተጣላቻቸው እነ ሳውዲአረብያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን በምክንያትነት የሚያስቀምጡ አሉ።


አሁን ይህ መሬት ለበርካታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሰጠቱን ሰምተናል። በምን መልኩ እንደተሰጠ ግን ግልጽ የሆነ ነገር የለም። በጨረታ ግን አለመሆኑን ተገንዝበናል። ምክንያቱም የከተማ አስተዳደሩ ያቋረጠውን የሊዝ መሬት ሽያጭ እስካሁን አልተጀመረም። በአዲስ አበባ ያለው የመሬት ማስተላለፍ ስራ ከበፊቱ ባልተሻለ ሁኔታ ለሙስና የተጋለጠና የተበላሸ ሆኗል ይላሉ ከስራው ጋር ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ምንጮች። [ዋዜማ ራዲዮ]

If you wish to contact Wazema Editors write to wazemaradio@gmail.com